በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቄለም ወለጋ ውስጥ ዛሬም ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፁ


ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

በኦሮምያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ ወረዳና ቀበሌውን ባልጠቀሱት አካባቢ በተፈፀመ ጥቃት “ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ ማምሻውን በማኅበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ላይ ባወጡት ፅሁፍ አስታውቀዋል።

"በኦሮምያ ክልል፣ ቄለም ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ ዜጎች ጭፍጨፋ ተፈፅሞባቸዋል" የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅሁፍ የተገደለውን ሰው ብዛት አልገለፀም።

በሌላ በኩል ጥቃቱ የተፈፀመው በቄለም ወለጋ ዞን፣ ሐዋ ገላን ወረዳ ውስጥ በሚገኝ መንደር ሃያ ተብሎ የሚጠራ አካባቢ መሆኑንና ቢያንስ ሰባ ሰው ሳይገደል እንዳልቀረ ከተገደሉት መካከል “ቤተሰቦቼ ይገኙባቸዋል” ያሉ አንድ የምዕራብ ወለጋ ነዋሪ ለቪኦኤ ተናግረዋል። የጠፋውን ህይወት ብዛት በሚመለከት ከአካባቢው ባለሥጣናትም ሆነ ከሌላ አካል የወጣ ማረጋገጫ ወይም የተለየ ቁጥር የለም።

በሰላማዊ ሰዎቹ ላይ ግድያውን የፈፀመው መንግሥቱ በሽብር የፈረጀውና ባለሥልጣናቱ “ሸኔ” እያሉ የሚጠሩት፤ “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት” እንደሚባል የሚናገረው ታጣቂ ቡድን መሆኑ ከዘመዶቻቸው እንደተነገራቸው እኝሁ የሟች ቤተሰብ አመልክተዋል።

መንግሥት በቡድኑ ላይ “እየወሰደ ነው” ያሉትን እርምጃ “አጠናክሮ እንደሚቀጥል” ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባያያዙት የኀዘን መልዕክታቸው ላይ ተናግረዋል።

ከሁለት ሣምንታት በፊት፤ ሰኔ 11 / 2014 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ጊምቢ ወረዳ፣ ቶሌ ቀበሌ ውስጥ በተፈፀመ የብሄር ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት 338 ሰላማዊ አማርኛ ተናጋሪ ነዋሪዎች መገደላቸውን መንግሥት ማስታወቁ ይታወሳል።

ክስ የሚሰማበት “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት” እንደሆነ የሚናገረው ታጣቂ ቡድን በመንግሥትም ሆነ በተጠቂ ቤተሰቦች የሚቀርቡበትን ውንጀላዎች በየወቅቱ እያስተባበለ ይገኛል።

XS
SM
MD
LG