በጋዛ የሚገኙ በመቶ የሚቆጠሩ ዒላማዎችን እንደደበደበች፣ እስራኤል፣ ዛሬ ማክሰኞ አስታውቃለች፡፡ ለሐማስ ጥቃት መልስ እንደኾነ የተገለጸውን ይህን ርምጃ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ፣ “ገና መጀመሩ ነው” ሲሉ ቀጣይነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
የቅዳሜውን ድንገተኛ ወረራ ተከትሎ፣ 1ሺሕ500 የሚደርስ የሐማስ ወታደሮች አስከሬን፣ በእስራኤል ግዛት ውስጥ እንደተገኘና ከትላንት ሰኞ ወዲህ የሐማስ ወታደሮች ወደ ግዛታቸው ዘልቀው እንዳልገቡ፣ ወታደራዊ ቃል አቀባዩ ሪቻርድ ሄክት ተናግረዋል።
በእስራኤል ጥቃት ዒላማ ውስጥ ከገቡት ውስጥ፣ በጋዛ ከተማ ሪማል የተሰኘው አካባቢ አንዱ ነው፡፡ በዚኽም፣ የሐማስ የሚኒስቴር መ/ቤቶች እና የመንግሥት ሕንፃዎች እንደሚገኙበት ታውቋል።
ቤንያሚን ናታንያሁ ትላንት ምሽት በሰጡት መግለጫ፣ “በቀጣይ ቀናት በጠላቶቻችን ላይ የምንወስደውን ርምጃ ለትውልድ የሚያስታውሱት ይኾናል፤” ሲሉ ክብደቱን ጠቁመዋል፡፡
የእስራኤል ጦር፣ 300 ሺሕ ተጠባባቂ ኀይሉን እንዳንቀሳቀሰ አስታውቋል።
እስራኤል፣ ያለማስጠንቀቂያ በጋዛ የሚኖሩ ሲቪሎችን ዒላማ ባደረገች ቁጥር፣ ከታገቱት 150 እስራኤላውያን ውስጥ አንድ እንደሚገድሉ፣ የሐማስ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ዝተዋል።
እስራኤል ጋዛን “ሙሉ ለሙሉ እንደምትከብ፣” የፍልስጥኤምን ግዛት የኤሌክትሪክ፣ የምግብ፣ የውኃ እና የነዳጅ አቅርቦት እንደምትዘጋ፣ የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት፣ ትላንት በቪዲዮ በለቀቁት መግለጫቸው አስታውቀዋል። ይህ አስተያየታቸው፣ ከሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖች ተቃውሞ ገጥሞታል። ሰዎችን በጅምላ መቅጣት፣ የዓለም አቀፍ ሕግን እንደሚጥስ፣ የሰብአዊ ቡድኖቹ አስጠንቅቀዋል።
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ለዜና ሰዎች ሲናገሩ፣ የእስራኤልን የጸጥታ ስጋት ቢረዱም፣ ወታደራዊ ዘመቻዎች የሰብአዊ ሕግን ባገናዘበ መልክ መካሔድ ይኖርባቸዋል፤ ብለዋል። ሲቪሎች ጥበቃ ሊደረግላቸውና የሲቪል መሠረተ ልማቶችም ዒላማ መኾን እንደሌለባቸው ጉቴሬዥ ተናግረዋል።
“እስራኤል ጋዛን ሙሉ ለሙሉ ከብባ፣ የኤሌክትሪክ፣ የምግብ፣ የውኃ እና የነዳጅ አቅርቦትን እንደምትዘጋ ማስታወቋ አሳስቦኛል፤” ብለዋል ጉቴሬዥ። “የጋዛ ሰብአዊ ኹኔታ ከተባባሰው ግጭት በፊትም ቢኾን አሳሳቢ ነበር። አሁን ደግሞ ይበልጥ ተበላሽቷል፤” ሲሉ፣ አክለዋል ጉቴሬዥ።
እስከ ትላንት ሰኞ ድረስ፣ የሟቹች ቁጥር በእስራኤል ወገን 900 ሲደርስ፣ በጋዛ ወገን ደግሞ 687 እንደኾነ ተገልጿል። ቁጥሩ ከዚኽም እንደሚያሻቅብ ይጠበቃል። በሁለቱም ወገን ስድስት ሺሕ ሰዎች እንደተጎዱ ተነግሯል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ 11 አሜሪካውያን በግጭቱ ሕይወታቸውን እንዳጡ ተናግረዋል።
በእስራኤል ሕይወታቸውን ካጡት ውስጥ፥ የአርጀንቲና፣ የእንግሊዝ፣ የካምቦዲያ፣ የፈረንሳይ፣ የኔፓል፣ የታይላንድ እና የዩክሬን ዜጎች እንደሚገኙበት፣ የየሀገራቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
አንዳንድ መንግሥታት፣ ዜጎቻቸውን ከእስራኤል በማስወጣት ላይ ይገኛሉ። 300 የሚደርሱ ደቡብ ኮሪያውያን፣ ነገ ረቡዕ ወደ ሀገራቸው እንደሚገቡ ይጠበቃል፤ ሲሉ፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ለቪኦኤ የኮሪያ አገልግሎት ተናግረዋል።
ተመድ በበኩሉ፣ በጋዛ ከሚኖሩት 2ነጥብ3 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ፣ 187 ሺሕ የሚኾኑት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንደኾኑ አስታውቋል።
የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የጣሊያንና የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ባወጡት የጋራ የአቋም መገለጫ፣ “እስራኤልን በአንድነት እንደግፋለን፤ የሐማስን ዘግናኝ የሽብር ድርጊት በማያሻማ ኹኔታ እናወግዛለን፤” ብለዋል።
“ኹላችንም የፍልስጥኤምን ሕዝብ ሕጋዊ መሻት እንገነዘባለን። የእስራኤላውያንንም ኾነ የፍልስጥኤማውያን ነጻነት እና ፍትሕ፣ በእኩል እና በተመሳሳይ እንደግፋለን። ሐማስ ግን፣ እነዚኽን የሕዝብ ፍላጎቶች አይወክልም። ለፍልስጥኤም ሕዝብ ምንም አያስገኝም። ይልቁንም ተጨማሪ ሽብር እና ደም መፋሰስን ያመጣል፤” ብለዋል ሀገራቱ በመግለጫቸው።
የቀድሞ የናታንያሁ ጽ/ቤት ሓላፊ አሪ ሀሮው ለቪኦኤ ዲዋ አገልግሎት ሲናገሩ፣ “ሐማስ ጥቃቱን ለእስራኤል ቅዱስ በኾነው ቀን በማድረጉ፣ እስራኤል ወደ ጦርነት ከመግባት ውጪ አማራጭ አልነበራትም፤” ብለዋል።
ሁለቱም ክፉዎች ናቸው፡፡ ልዩነታቸው አንዱ እስራኤልን ያጠቃ የሽብር ቡድን ሲኾን፣ ሌላው በዩክሬን ላይ ጥቃት የሰነዘረ መንግሥታዊ አሸባሪ መኾኑ ነው፤”
“ይህ፣ እስራኤል ያቀደችው ወይም የፈለገችው ነገር አይደለም። ይኹንና አንድ ጊዜ ጦርነት ታውጆብን ወደዚኽ ግጭት ተጎትተን ከገባን፣ ግባችን አንድ እና ግልጽ ነው፤ እስራኤል ወደፊት ተመሳሳይ ነገር እንዳይገጥማት፣ በጋዛ ያለውን የሽብር መሠረተ ልማት እስከ ወዲያኛው ማፍረስ ነው፤” ብለዋል ሀሮው።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው፣ ሐማስ በእስራኤል ላይ የፈጸመውን ጥቃት፣ ሩሲያ በአገራቸው ላይ ከፈጸመችው ጥቃት ጋራ አመሳስለውታል።
“ሁለቱም ክፉዎች ናቸው፡፡ ልዩነታቸው አንዱ እስራኤልን ያጠቃ የሽብር ቡድን ሲኾን፣ ሌላው በዩክሬን ላይ ጥቃት የሰነዘረ መንግሥታዊ አሸባሪ መኾኑ ነው፤” ብለዋል ዜለንስኪ፣ ኮፐንሃገን ውስጥ እየተካሔደ ላለው የኔቶ ወታደራዊ ስብሰባ በላኩት የቪዲዮ መልዕክት።
በዋሽንግተን ተቋም፣ የቅርብ ምሥራቅ ፖሊሲ ተመራማሪው ጌይት አል ኦማሪ ለቪኦኤ እንደተናገሩት፣ ሩሲያ፥ የእስራኤል እና ሐማስን ግጭት፣ ዩክሬን ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዳታገኝ ትጠቀምበታለች፤ ብለዋል።
“እስራኤል ጦርነቱን፣ የሲቪሎችን ጉዳት በሚቀንስ መልኩ ካከናወነች፣ የዓለም አቀፍ ድጋፍን ማግኘት እንደምትቀጥል አምናለኹ፤” ብለዋል አል ማሪ። “ነገር ግን፣ ያልተገባ ኃይል የምትጠቀም ከኾነ፣ ነገሮች ይቀየራሉ። በዚኽ መሀል፣ ሩሲያ ያለውን ዓለም አቀፍ ትብብር ለማፍረስ ትሞክራለች፤ ቻይናም እንዲሁ። ይህ አሜሪካም የምትፈተንበት ይኾናል፤” ሲሉ አክለዋል አል ማሪ።
መድረክ / ፎረም