ድንበር የለሽ ሃኪሞች ቡድን የአጣዳፊ ጉዳዮች ኃላፊዋ ቴራ ኖልን በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ድርቁ ያስከተለውን ችግርና ያንዣበበውን አደጋ ተዘዋውረው ተመልክተው ከጥቂት ቀናት በፊት ወደ አምስተርዳም መመለሳቸውን ገልፀውልኛል። ሁኔታውን ያስረዱትም በዐይን እማኝነት ጭምር ነው።
የሃኪሞች ቡድንኑ በሶማሌ ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ ለተጎዱ ሕፃናት የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ 12 ዓመታት አስቆጥሯል ይላሉ- ቴራ ኖልን። ነገር ግን ቡድኑ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲሰጥ ከነበርው አገልግሎት ጋር ሲያነፃፅረው ግን የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ሕፃናት ቁጥር በዐሥር እጥፍ ጨምሯል።
ሕፃናቱ በድርቁ ምክኒያት ባጋጠመ የተመጣጠነ የምግብና የመጠጥ ውሃ ማጣት በተጨማሪም ይህን ተክለትሎ በገባው የአተት ወረርሽኝና አቅም ማነስ ምክኒያት በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱበትን የዶሎ ዞንን ጨምሮ በተለያዩ ወረዳዎች የሕክምና ማእከላት አቋቁመው ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 8 ሺሕ ሕፃናትን ለመርዳት እየሞከሩ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከእነዚህ ውስጥ በሕክምና መትርፍ ያልቻሉ ሕፃናት በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑንም ገልፀዋል
“በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ነው። ዕድሜያቸው አምስት ዓመት ያልሞላ 68 ሕጻናት አስቀድሜ በጠቀስኳቸው የሕክምና ማእከላት በሰኔ ወር ብቻ ሕይወታቸው አልፏል። ሰኔ ወር ገና አለማለቁን ስናስብ፤ ሁኔታው ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው። በእርግጥ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት የምናደርገው ጥረት እንዳለ ሆኖ፤ እነዚህን ሕጻናት ለማዳን አለመቻላችን በተለይ ሁኔታው እጅግ መጠነ ሰፊና ቀሳፊ መሆኑ ጋር ስራውን ከባድ ያደርገዋል። በርካታ ሕጻናትን ለመድረስና ህክምና ለመስጠት ካሉብን ፈተናዎች አንጻር፤ ጥቂቶችን ብቻ ደርሰን የህክምና ርዳታ ማድረግ ላይ ማተኮራችን፤ መድረስ የሚገባንን ያህል ሰፊ የአገልግሎት ሽፋን አለማቅረባችን በእጅጉ ይረብሸናል። ለጥቂቶች አጠቃላይ የህክምና እርዳታ በማድረሰና አገግሎትን በማስፋት መካከል እንድንመርጥ መሆኑ የሚያሳዝን ነው።” ብለዋል።
ጽዮን ግርማ የድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን የአጣዳፊ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑትን ቴራ ኖልን አነጋግራ ያጠናቀረችውን ዘገባ ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ