የዩናይትድ ስቴትሷ ከፍተኛ ዲፕሎማት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ሰላምንና ጸጥታን ጨምሮ በኢትዮጵያ እና በአካባቢው ሀገራት ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ላይ ለመታደም ኢትዮጵያ የገቡት ሞሊ ፊ፣ ከኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ጋራም በሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡
የአህጉራዊ ኅብረቱ መቀመጫ የኾነችውን ኢትዮጵያንና አንዳንድ ጎረቤቶቿን ጨምሮ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በደኅንነት ቀውስ ውስጥ እያሉ የሚካሔደው የኅብረቱ ጉባኤ በአዲስ አበባ ቀጥሏል፡፡ የኅብረቱ መሪ ቃል ትምህርት ተኮር ቢኾንም፣ ጉባኤው በአህጉሪቱ ቀውሶች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ እንደሚወያይ፣ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ገልጸዋል፡፡
አማርኛ የኅብረቱ ይፋዊ የሥራ ቋንቋ እንዲኾን፣ ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ጠይቃለች፡፡ ለደኅንነቷም መጠናከር ከኅብረቱ እና ሌሎች አጋሮች ጋራ ለመሥራት ዝግጁ እንደኾነች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት 37ኛ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የሚገኙት በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ፣ ትላንት ረቡዕ፣ የካቲት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች በምትገኝበት በዚህ ወቅት፣ ሁለቱ አካላት “የኢትዮጵያ እና የቀጣናው ሰላም እና ጸጥታ” በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ እንደተወያዩ፣ ሞሊ ፊ አስታውቀዋል፡፡
በአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ የኤክስ ገጽ ላይ ውይይቱ ፍሬያማ እንደነበር የገለጹት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ፣ “የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ ደኅንነት፣ ዴሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብቶች እና ብልጽግና” ዋና ትኩረቶች እንደነበሩ አስፍረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም፣ “በአህጉራዊ እና በባለብዙ ወገን ጉዳዮች ላይ ተወያይተናል፤” ሲሉ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል፡፡ በውይይቱ ላይ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመርም ተገኝተዋል፡፡
ሚስ ፊ፣ በ37ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤም ላይ የሚገኙ ሲኾን፣ ጉባኤው በሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ኅብረቱ አስታውቋል፡፡
የዘንድሮው ጉባኤ “በትምህርት” ላይ እንደሚያተኩር በመሪ ቃሉ ቢገለጽም፣ ለመሪዎቹ ጉባኤ አጀንዳ የሚዘጋጅበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ፣ ትላንት ረቡዕ ሲጀመር፣ የኅብረቱ ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በአንዳንድ አባል ሀገራት ያሉ የጸጥታ ችግሮች የጋራ መፍትሔ እንደሚሹ አሳስበዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካዎቹን ሱዳንና ሶማሊያን ጨምሮ፣ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ያለው ቀውስ አሳሳቢ እንደኾነ የገለጹት ሊቀ መንበሩ፣ “የወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አባዜ ማገርሸቱ፣ ከምርጫ በፊት እና በድኅረ ምርጫ ያለው ብጥብጥ፣ ከጦርነት ጋራ የተያያዙ ሰብአዊ ቀውሶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ውጤቶች፣ ሁሉም እኛን በጣም የሚያሳስቡን ችግሮች ናቸው።”ብለዋል።
አክለውም “የምንኮራባትን የተዋሐደች አፍሪካ የመፍጠር ጭላንጭሎችን እንዳያከስሙ በከፍተኛ ኹኔታ የምንሰጋባቸው ችግሮቻችን ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
በዚኹ የሚኒስትሮቹ ጉባኤ ላይ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ሰነድ ከተጻፈባቸው ቋንቋዎች አንዱ የኾነው አማርኛ፣ የአፍሪካ ኅብረት ይፋዊ የሥራ ቋንቋ እንዲኾን፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ ጠይቀዋል፡፡ የፕሪቶርያን የሰላም ስምምነትም በማሳያነት የጠቀሱት አቶ ታዬ፣ የአፍሪካ ኅብረት በአህጉሪቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላሟን ለማጽናት ከኅብረቱ እና ከአጋር አካላት ጋራ በትብብር መሥራቷን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡
“የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ሰላምን ለማጠናከር ከአፍሪካ ኅብረት እና ከኅብረቱ የክትትል አካል ጋራ መሥራቱን ቀጥሏል።” ያሉት አምባሳደር ታዬ “ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የምክክር ሒደት፣ ይበልጥ መረጋጋትን ለማጎልበት አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ የአገራችንን መረጋጋት ለማጠናከር፣ ከሌሎች ሀገራት ጋራ በቅርበት ለመሥራትም ቁርጠኞች ነን፡፡” ብለዋል።
ምንም እንኳን፣ ደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ቢያበቃም፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ ቦታዎች የትጥቅ ግጭቶች በቀጠሉበት ድባብ ውስጥ ነው፣ ኢትዮጵያ የአህጉራዊ ኅብረቱን የመሪዎች ጉባኤ በማስተናገድ ላይ ያለችው፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ ቀውሶችን ጨምሮ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ የተወያዩት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሞሊ ፊ፣ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ጋራም በኢትዮጵያ ባለው የሰብአዊ መብቶች ኹኔታ ላይም ተወያይተዋል፡፡
የመርዓዊ ከተማን ጨምሮ በአማራ ክልል ሦስት ስፍራዎች፣ ባለፈው ጥር ወር፣ በትንሹ 66 ሰዎች በመንግሥት ኃይሎች ከሕግ ውጭ እንደተገደሉ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የካቲት 5 ቀን ባወጣው መግለጫ ሲያስታውቅ፣ በጥቃቱ፣ “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ቢያንስ 45 ሲቪሎች መገደላቸውን መግለጹ ይታወቃል፡፡ የአሜሪካ መንግሥትም ግድያው እንዳሳሰበው ገልጾ ገለልተኛ ምርመራ ያለገደብ እንዲደረግ መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ይኸው ጉዳይ፣ በሞሊ ፊ እና በዶ/ር ዳንኤል ውይይት ላይ ተነሥቶ እንደኾን፣ ሁለቱም አካላት ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን በጠቀሱበት የኤክስ ገጻቸው አስተያየት ላይ አልገለጹም፡፡
የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትሯ ሞሊ ፊ፣ ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ጋራም የተነጋገሩ ሲኾን፣ “በኢትዮጵያ መረጋጋትንና ሰላምን ለማስፈን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማጠናከር አስፈላጊ ነው፤” ብለዋል። ኢኮኖሚውን ለማሳደግና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚደረጉ ማሻሻያዎችም በውይይታቸው ላይ እንደተነሡ፣ ረዳት ሚኒስትሯ በመሥሪያ ቤታቸው የኤክስ ገጽ ላይ ገልጸው፣ ለዚኽም ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና ከዓለም ባንክ ጋራ በትብብር መሥራቷን መቀጠል እንዳለባት አስረድተዋል፡፡
ለሁለት ቀናት የተካሔደው 44ኛው የአፍሪካ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ዛሬ ሲጠናቀቅ፣ 37ኛው የመሪዎች ጉባኤ ደግሞ የፊታችን ቅዳሜ እና እሑድ ይካሔዳል፡፡
መድረክ / ፎረም