በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ኦክቶበር ቴን” - አዲስ ምዕራፍ ለአሮጌዪቱ ላይቤሪያ


ላይቤሪያዊያን መጭ ፕሬዚዳንታቸውንና እንደራሴዎቻቸውን ለመምረጥ ይወጣሉ። አሁን ያሉት ፕሬዚዳንት ኤን ጆንሰን ሰርሊፍ ለሁለት የሥልጣን ዘመናት ካገለገሉ በኋላ በያዝነው የአውሮፓ ዓመት መጨረሻ ይሰናበታሉ። ፉክክሮቹ ሁሉ እያተኮሩ ያሉት ሃገሪቱን በእጅጉ ባደቀቃት ኢቦላ ወረርሽኝ ምክንያት በተጎዱት መሠረተ ልማትና የጤና ጥበቃ አገልግሎት ላይ ነው።

የዘንድሮ የላይቤሪያ ምርጫ ለዚህች እጅግ አንጋፋ አፍሪካዊት ሃገር ያለፉ 73 ዓምታት ታሪካዊ ነው የሚሆነው፤ መስከረም 30፣ ላይቤሪያዊያን ከእንግዲህ “ኦክቶበር ቴን” እያሉ በታሪካቸው መድብሎች የሚጠቅሷት ዕለት ትሆናለች።

ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ ዘንድሮ ለሰላማዊ የሥልጣን ቅብብሎሽ መንገድ ከፍተው ይሰናበታሉ። እንዲህ ዓይነት ለውጥ ሞንሮቪያን ላለፉት ሰባት አሠርት ዓመታት አላየችም።

ፕሬዚዳንት ሰርሊፍን ለመተካት ‘እኔ እሻላለሁ’ ያሉ ሃያ ዕጩዎች የምረጡኝ ዘመቻዎቻቸውን አጠናቅቀው ተሰልፈዋል።

ሰባ ሦስት መቀመጫዎች ላሉት የላይቤሪያ የተወካዮች ምክር ቤት አንድ ሺህ ዕጩዎች ይወዳደራሉ።

በቻርልስ ቴይለር አስተዳደር የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ተለዋጭ ሰብሳቢ የነበሩት ቻርልስ ብሩምስካይን፤ ሎንስታር የሚባለው የሞባይል ስልክ ኩባንያ መሥራችና የቴይለር ዘመን የባሕር ጉዳዮች ሚኒስትር ቤኖኒ ዬሬይ፤ ስመ ገናናው የእግር ኳስ ኮከብና የሞንትሴራዶ ሴናተር ጆርጅ ዊአ፤ የአሁኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆዜፍ ቦአካዪ፤ የቀድሞ የኮካ ኮላ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ፣ አሁን የአማራጭ ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲው አሌክሳንደር ከሚንግስ ለፕሬዚዳንታዊው ሥልጣን ከሚጋፉት መካከል ናቸው።

ከአራት ሚሊየኑ የሃገሪቱ ሕዝብ በአምስት ሺህ ጣቢያዎች ላይ ለሚፈቅደው ካርድ ሊጥል ነገ የሚወጣው ላይቤሪያዊ ሁለት ሚሊየን የተመዘገበ ድምፅ ሰጭ ነው።

የምርጫው ውጤት ከሁለት ሣምንት በኋላ ጥቅምት 15 በይፋ ይገለፃል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

“ኦክቶበር ቴን” - አዲስ ምዕራፍ ለአሮጌዪቱ ላይቤሪያ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:01 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG