በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፓርቲዎች ለእሁዱ ምርጫ የመጨረሻ ቅስቀሳቸውን አደረጉ


ከሀሙስ ጀምሮ የምርጫ ቅስቀሳ ማከናወን አይቻልም።

እሁድ በሚደረገው የሀገር አቀፍና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በዛሬውለት የምረጡኝ ዘመቻቸውን አቁመዋል።

አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ የክልል ከተማዎች በከፍተኛ ስብሰባዎችና በየመንገዱ በተሰናዱ የምረጡኝ ቅስቀሳዎች ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች መልእክቶቻቸውን ሲያሰሙ ውለዋል። ቅስቀሳው ከ12 ሰአት ጀምሮ የቆመ ሲሆን ከአሁን በኋላ ስብሰባ ማካሄድ እንደማይቻል የምርጫ ስምምነቱ ይደነግጋል።

በአምቦ ውሎአቸውን ሲቀሰቅሱ ውለው ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ-መድረክ ተወዳዳሪ ዶክተር መረራ ጉዲና ፓርቲያቸው ለመራጮች ባቀረበው የመጨረሻ የምረጡኝ ዘመቻ “መንግስት ላለፉት 18 አመታት ሀቀኛ ፌዴራላዊ ስርአትን እፈጥራለሁ ሲል ነበር፤ እስካሁን ድረስ ያለው የውሸት ፌዴራሊዝም ነው” ብለዋል።

“እኛ ብንመረጥ ሀቀኛ የፌደራላዊ አስተዳደር እንፈጥራለን፤ እኛ ሀቀኛ የዴሞክራሲ አስተዳደርን በኢትዮጵያ እንፈጥራለን፤ ከተመረጥን የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የራሳቸው የመሬት ባለቤት ይሆናሉ፤ ብንመረጥ ለገበሬውም ለከተማውም ግብር እንቀንሳለን፤ የማዳበሪያ ዋጋ ይቀነሳል፤ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የጫነውን አምባገነናዊ አስተዳደር በህዝብ ድምጽ እናወርዳለን” ሲሉ መረራ ጉዲና የፓርቲያቸውን ራእይ አስቀምጠው መራጮች ድምጽ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።

ባለፉት 18 አመታት በመሰረተ-ልማት ግንባታ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት በኢትዮጵያ ልማታዊ መንግስት ለመመስረት እንደቻለ የሚናገረው የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ እጩና አለማየሁ ተገኑ የማእድንና ኤነርጂ ሚኒስትር ናቸው።

አለማየሁ ተገኑ የማእድንና ኤነርጂ ሚኒስትር
አለማየሁ ተገኑ የማእድንና ኤነርጂ ሚኒስትር

“የተፈተነና ሀገሪቷን ከድህነት አውጥቶ የመካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ የሚያሰልፍ ፖሊሲዎችን ይዟል” ይላሉ ስለፓርቲያቸው ኢህአዴግ ሲናገሩ። “ተቃዋሚዎች ከዚህ አኳያ ምንም ያቀረቡት አማራጭ እንደሌለ መራጮቻችን ተገንዝበዋል”

ኢህአዴግ ከፍተኛ ፉክክር የሚጠብቀው የስምንት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት ከሆነው መድረክ ነው። መድረክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ልዩነትን አቻችሎ መቀናጀቱናና በምርጫ የሚገኙ ውጤቶችን አስከብሮ ለዴሞክራሲ ሂደቱ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የሚናገሩት ዶክተር ሀይሉ አርአያ በአዲስ አበባ በወረዳ 23 ይሳተፋሉ።

በዚህ ወረዳ የቀደሞ የትግል አጋራቸው አቶ ሀይሉ ሻውል ተሳታፊ ናቸው። አቶ ሀይሉ ሻውል ፉክክሩ እንዳለ ሆኖ “ድምጽ መስጠቱን ለህዝቡ ትተን እርስ በእርስ ፍጥጫ ላይ ላለመግባት ወስነናል” ያላሉ። በዚህ ወረዳ ባለፈው ምርጫ ተወዳድረው የተመረጡት አቶ ሀይሉ ሻውል ሲሆኑ፤ በእሁዱ ምርጫ የወረዳው ህዝብ እንደሚመርጣቸው በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

የማእድንና ኤነርጂ ሚኒስትሩ አቶ አለማየሁ ተገኑ በሚወዳደሩበት ወረዳ 18 ከፍተኛ ፉክክር ይኖራል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲው ሙሼ ሰሙና የቀደሞው ፕሬዝደንት ነጋሶ ጊዳዳ በዚህ የምርጫ ጣቢያ ለፓርላማ መቀመጫ ይፋለማሉ።

(እጩ ተወዳዳሪዎቹ ያደረጉትን የማጠቃለያ ዘመቻ ከአንደበታቸው ለመስማት በገጹ በስተቀኝ የድምጽ ዘገባውን ያዳምጡ)

XS
SM
MD
LG