በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መከላከያ እና ፋኖ በላሊበላ ከተማ ውጊያ እንዳካሄዱ ነዋሪዎች ተናገሩ


ፎቶ ፋይል፦ ላሊበላ ከተማ
ፎቶ ፋይል፦ ላሊበላ ከተማ

በፌዴራል መንግስት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በታሪካዊቷ ላሊበላ ከተማ ዛሬ ረቡዕ ውጊያ ተካሂዶ እንደነበር የከተማዋን ነዋሪዎች ጠቅሶ የኤኤፍፒ ዜና ወኪል ዘግቧል።

ውቅር አብያተ ቤተክርስቲያናት የያዘችው እና በዩኔስኮ ቅርስነት የተመዘገበችው የላሊበላ ከተማ፣ በሁለቱ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት የውጊያ አውድማ ስትሆን የመጀመሪያ ግዜ አይደለም።

“ውጊያው የጀመረው ዛሬ ጠዋት 2 ሰዓት አካባቢ ነው። ፋኖ የተወሰነ የከተማዋን ክፍል የተቆጣጠረ ይመስላል። የተወሰኑ ተዋጊዎቹን ዋናው መንገድ ላይ አይቻለሁ” ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የላሊበላ ቤ/ክ ዲያቆን ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

“የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አሁንም የአየር ማረፊያውን እንደተቆጣጠረ ነው” ሲሉ አክለዋል ዲያቆኑ። ውጊያው እንደቀጠለ እና የተወሰኑ ሲቪሎችም እንደተጎዱ ጨምረው ገልጸዋል።

የፌዴራል መንግስት ወኪሎችም ሆኑ የመከላከያ ቃል አቀባይ አስተያየት እንዲሰጡ ለተላከላቸው መልዕክት መልስ እንዳልሰጡ ዜና ወኪሉ ገልጿል።

ትናንት ምሽት ፋኖ በአራት አቅጣጫዎች ወደ ላሊበላ ከተማ እንዳመራ እና ዛሬ ጠዋት 2 ሰዓት አካባቢ ውጊያ እንደተጀመረ ሌላ የከተማው ነዋሪ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

በላሊበላ ውቅር አብያተ ቤተክርስቲያናት አካባባቢ ውጊያ እንዳልተካሄደ ነዋሪው ጨምረው ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ለጋዜጠኞች ክፍት ባለመሆኑ፣ ሁኔታውን በገለልተኛ መንገድ ለማጣራት አዳጋች መሆኑን ዜና ወኪሉ ገልጿል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG