በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዐማራ ክልል በሚካሄድው ጦርነት የላሊበላ ውቅር አብያተ መቅደሶች አደጋ ላይ ወደቀዋል


 የላሊበላ ከተማ ውቅር አብያተ መቅደሶች
የላሊበላ ከተማ ውቅር አብያተ መቅደሶች

በዐማራ ክልል ሰሜናዊ ዞኖች፣ በመከላከያ ኀይል እና በፋኖ ታጣቂ ቡድን መካከል ዳግም የተቀሰቀሰው ዐዲስ ውጊያ፣ በተቀደሰችው የላሊበላ ከተማ የሚገኙትን ውቅር አብያተ መቅደሶች አደጋ ላይ ጥሏል፤ የሚል ስጋት በነዋሪዎች ዘንድ ፈጥሯል፤ ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።

በአጎራባቹ የትግራይ ክልል ተቀስቅሶ በዐማራ እና በአፋር ክልሎች ተስፋፍቶ የነበረው የሁለት ዓመት ጦርነት ካበቃ ወዲህ፣ በዐማራ ክልል የቀጠለው ግጭት፣ የኢትዮጵያ አሳሳቢ የጸጥታ ችግር ኾኗል። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር፣ የፋኖ ታጣቂዎች፣ ላሊበላንና የክልሉን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ጎንደርን ለቀናት ተቆጣጥረው ነበር።

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ የፋኖ ታጣቂዎች ከመከላከያ ሠራዊት ጎን ቆመው ቢዋጉም፣ በሚያዝያ ወር የፌዴራል መንግሥት፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የጸጥታ ኃይሎችን፣ ወደ ፖሊስ እና የጦር ሠራዊቱ ለማዋሐድ መወሰኑን ተከትሎ፣ በሁለቱ መካከል የነበረው ግንኙነት ሻክሯል።

ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ ለውቅር አብያተ መቅደሶቹ ቅርብ ከኾኑ ስፍራዎች፣ የጦር ኀይሉ ወታደሮች 11 ጊዜ ከባድ መሣሪያዎችን እንደተኮሱ፣ አንድ ዲያቆን አስታውቋል። ከመሣሪያዎቹ የሚነሣ አደገኛ እና ጎጂ ንዝረትም፣ በ12ኛው እና በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተሠሩ አስደናቂ አብያተ መቅደሶች አንዱ የኾነውን ቅርስ አደጋ ላይ ጥለውታል።

ሊደርስበት የሚችለውን ጥቃት በመፍራት ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀው ዲያቆን፣ “የመሣሪያዎቹ ተኩስ የሚፈጥረው መንቀጥቀጥ፣ አብያተ ክርስቲያናቱን እየጎዳ ነው፤” ብሏል።

ሁለት የከተማዋ ነዋሪዎችም፣ ዐዲስ ግጭት መቀስቀሱን አረጋግጠዋል። አንደኛው ነዋሪ፣ ከላሊበላ ከተማ አቅራቢያ እና ከአየር ማረፊያው አካባቢ የሰፈረው የኢትዮጵያ ጦር፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ውጊያ መጀመሩንና ከተማዋን ቁልቁል ከሚያሳየው ተራራ ላይ በመኾን ከባድ መሣሪያዎች መተኮሱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ፣ የመከላከያ ጦር እና የዐማራ ክልል አስተዳደር፣ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ተጠይቀው ምላሽ አልሰጡም።

በላሊበላ አካባቢ ተወልደው ያደጉትና አሁን በአሜሪካ የሚኖሩት ፖለቲከኛው ልደቱ አያሌው፣ ውቅር አብያተ መቅደሶቹ፣ በጦር መሣሪያ ሊመቱና ሊወድሙ ይችላሉ፤ የሚል ስጋቱን ገልጿል። ልደቱ፣ ትላንት ሰኞ ባወጡት መግለጫ፣ “አብያተ ክርስቲያናቱ ጥንቃቄ በጎደለው የከባድ መሣሪያ ተኩስ ምክንያት ሊመቱና ሊወድሙ በሚችሉበት አደጋ ውስጥ ናቸው፤” ብሏል።

ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ፣ ከአንድ አለት(ቋጥኝ) ተፈልፍለው የተሠሩ ናቸው። እ.አ.አ በ1978 ስፍራውን በዓለም ቅርስነት የመዘገበው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የኦቶማን ቱርኮች መስፋፋት ክርስቲያን ምዕመናን ወደ ቅድስት ሀገር የሚያደርጉትን ጉዞ በማስተጓጎሉ፣ “ዳግሚት ኢየሩሳሌምን" በኢትዮጵያ ለመፍጠር የታነፀ እንደኾነ አመልክቷል።

በዐማራ ክልል የሚካሔደው ጦርነት በጀመረበት ወር፣ ቢያንስ 183 ሰዎች እንደተገደሉ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ነሐሴ ወር ላይ አስታውቆ ነበር። ኾኖም በክልሉ፣ የኢንተርኔት ግንኙነቶች በመቋረጣቸው፣ ሮይተርስ በክልሉ ስላለው ወቅታዊ ኹኔታ ግልጽ መረጃ ለማግኘት እንደተቸገረ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ “በዐማራ ክልል ለወራት የቀጠለው የትጥቅ ግጭት ዐውድ እና አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች አንድምታ” በሚል ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፣ ግጭቱ በተካሔደባቸው አካባቢዎች፣ የመንግሥት የጸጥታ አካላት፣ በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪል ሰዎች ውስጥ፣ “ፋኖን ትደግፋላችኹ፤ ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችኹ፤ መሣሪያ አምጡ፤ የተኩስ ድምፅ ስለተሰማበት አቅጣጫ መረጃ ስጡ፤” በሚልና መሰል ምክንያቶች፣ ከሕግ ውጭ የኾኑ ግድያዎች እንደተፈጸሙ የሚያሳዩ ተኣማኒ መረጃዎች እንደደረሱትም ገልጿል፡፡

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት፣ “ሚዛናዊነት የጎደለውና በትክክለኛ መረጃ ላይ ያልተመሠረተ ነው፤” ሲል ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል::

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG