በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቆቦ ከተማ ተቃውሞ፣ሞት፣ግጭትና ቃጠሎ


በቆቦ ከተማ ከተቃውሞው በኋላ የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ በዋትስ አፕ የተላከልን ፎቶ ነው
በቆቦ ከተማ ከተቃውሞው በኋላ የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ በዋትስ አፕ የተላከልን ፎቶ ነው

በቆቦ ከተማ ለሁለት ቀናት በተደረገ ተቃውሞና ግጭት እስካሁን ሰባት ሰዎች መሞታቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል። ከተቃውሞው በኋላ በርካታ ንብረቶች በቃጠሎ መውደማቸንና በአሁኑ ሰዓት ከተማው በመከላከያ ሠራዊት በቁጥጥር ስር መዋሉን ነግረውናል።

በቆቦ ከተማ ተቃውሞ፣ሞት፣ግጭትና ቃጠሎ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:35 0:00

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ግጭቱ የተቀሰቀሰው፤ “በወልዲያ ከተማ ንጹኃንን የገደሉ የመንግሥት ታጣቂዎች ለፍርድ ይቅረቡ” እንዲሁም “በቆቦ ከተማ የታሰሩ ወጣቶች ይፈቱ” የሚሉ መፈክሮችን የሚያሰሙ የከተማው ነዋሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣታቸው ነው ብለውናል።

ሁኔታውን በቅርብ ሲከታተል እንደነበር የገለፀለን ወጣት እንደተናገረው፤ "እስካሁን እነርሱ ሰባት ገድለዋል። አንድ መከላከያም ሞቷል። እስካሁን በሄሊኮፕተር ነው ሲያሸብሩን የዋሉት።" በማለት ከተማው ውስጥ የመንግሥት ታጣቂ ሰራዊት መስፈሩን ይናገራል።

አያይዞም የከተማው ሕዝብ ከወልድያው ግድያ በተጨማሪ በከተማው ከኮማንድ ፖስቱ ጊዜ ጀምሮ የታሰሩ ወጣቶችን ጉዳይ ለመጠየቅ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ማቅናቱን ይናገራል። "እነሱ ይፈቱልኝ ብሎ ጥያቄ አቀረበ። ይባስ ብለው የከተማውን ሕዝብ ይደበድቡ ነበር። በዚህ ግዜ ሕዝቡ በነቂስ ወጣ የታሰሩትን ካስፈታ በኋላ መረጃ እየሰጡ ሲያስደበድቡን ነበር ያሉትን ሰዎች ቤት ንብረትና የመንግሥት ተቋማትን ማቃተል ጀመረ" ሲል የቆቦ ከተማውን ውሎ ይናገራል።

ተቃውሞው ወደ ግጭት ተቀይሮ ፤ የመንግሥት ተቋማትና መኪኖች፣ የእርሻ ልማት ድርጅቶች፣ የፓርቲ ጽቤት፣ የባለሃብቶች ንብረት፣ ዘንርን መሰርት ያደረገ ቤትና ንብረት መቃጠሉን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።

ሌላው በቆቦ ከተማ ተወልደው ያደጉና በተመሳሳይ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አዛውንት፤ "ከተማዋ የጦርነት ከተማ ሆናለች"ይላሉ።

በሌላ በኩል የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የቆቦ ከተማ ነዋሪዎች ንብረት መቃጠሉን ገልፀዋል። "ይህ እንዴት ሆነ ተገቢስ ነው ወይ?" በሚል የተጠየቁት አዛውንት ሲመልሱ፡-

"እያንዳንዱ ከታች ያለው የትግራይ ሕዝብ ሕወሓትን እንደታቦት ነው የሚያመልከው። በዚህም ምክኒያት አጋራችን አልሆነም። የኛን ብሶት እንደብሶት አላየውም። የኛን ጭቆና እንደጭቆና አላየውም። የኛን ባርነት እንደባርነት አላየውም። እነርሱ እንኳን ባይመቻቸው ሕወሓትን የሚነካባቸው ሰው አይወዱም። አብረን እየኖርን ገበያ ላይ ሲከለክሉን እንኳን 'አይሆንም' አይሉልንም። ስለዚህ ይህ የተጠራቀመ የዞረ ድምር ነው።" ብለዋል።

የመንግሥት ታጣቂዎች ለተቃውሞ በወጣው ሕዝብ ላይ በምድርና በአየር ጥቃት እንደፈፀሙባቸውና ሄሊኮፕተሮቹ አሁን ከመሸም በኋላ በከተማው አናት ላይ እየተዘዋወሩ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ መረጃ ለማግኘት የክልሉን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁና ሌሎች ባለሥልጣናትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ስልካቸው ስለማይነሳ አልተሳካልንም።

የዘገባውን ሙሉ ዝርዝር ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG