ኬንያ ውስጥ እአአ ካለፈው መጋቢት ጀምሮ በደረሰው አውዳሚ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 188 መድረሱን የሀገር አስተዳደር ሚኒስቴሩ ዛሬ አስታወቀ፡፡ እስካሁን ያልተገኙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን ሚኒስቴሩ አክሎ አስታውቋል፡፡
በኬንያ እና በሌሎችም የምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች በተከታታይ የጣለው ከባድ ዝናብ የብዙ ሰው ህይወት ለማጥፋቱም ሌላ ባስከተለው የከፍታ ቦታዎች መናድ ነዋሪዎችን ካለመጠጊያ አስቀርቷል፡፡ መንገዶችን፡ ድልድዮችን እና ሌላም የመሰረተ ልማት አውታሮችን አውድሟል፡፡
የኬንያው የሀገር አስተዳደር መግለጫ እንዳለው በጎርፍ አደጋው 125 ሰዎች የተጎዱ ሲሆን 90 ሠዎች የደረሱበት አልታወቀም፡፡ ትናንት ረቡዕም በዝነኛው የማሳይ ማራ የዱር አራዊት ፓርክ አካባቢ በጣለው ዝናብ ምክንያት አቅራቢያው ያለ ወንዝ ሞልቶ በመጥለቅለቁ 100 ጎብኚዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መውጫ አጥተዋል፡፡ የእርዳታ ሰራተኞች በአየር እና በየብስ ዘጠና ሰዎችን ለማውጣት እንደተቻለ የሚኒስቴሩ መግለጫ አመልክቷል፡፡
የኬንያ ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ የጦር ሰራዊቱ የጎርፍ አደጋ ላይ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን በሙሉ እንዲያወጣ አሰማራለሁ ያሉ ሲሆን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እና ተሟጋች ቡድኖች በበኩላቸውን የሩቶ መንግሥት የጎርፍ አደጋ እንደሚከሰት ማስጠንቀቂያ ቢደርሰውም በአግባቡ አልተዘጋጀበትም በማለት ወንጅለዋል፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዋች ዛሬ ባወጣው መግለጫ የኬኒያ መንግሥት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ከሚደርሱ አደጋዎች ህዝቡን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታኒያ የኬኒያን የጎርፍ ሁናቴ አስመልክተው ዜጎቻቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
መድረክ / ፎረም