በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኬንያ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ውድቅ ተደረገ


ኬንያ በቅርቡ ያካሄደችው ፕሬዘደንታዊ የምርጫ ሂደት ፍትሃዊ አልነበረም ሲል የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውጤቱን ውድቅ አድርጓል፤ ምርጫው በድጋሚ እንዲካሄድ ወስኗል።

ነሐሴ 2 / 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የኬንያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተቀማጩ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ማሸነፋቸው በምርጫ ኮሚሽኑ ቢታወጅም የተመራጩ ፕሬዚዳንት ተቀናቃኝ የሆኑት ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ ውጤቱን እንደማይቀበሉ በማሳወቅ ለሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ አስገብተው ነበር።

የዛሬውን የፍርድ ቤቱን ውሣኔ ያስተላለፉት ዳኛ ዴቪድ ማራጋ የሃገሪቱ የምርጫ ቦርድ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ህገመንግሥቱና የሃገሪቱ የምርጫ ሕግ በሚያዝዙት መሠረት ባለማካሄዱ ውጤቱ ውድቅ መደረጉን አስታውቋል።

“ነኀሴ 2 / 2009 ዓ.ም. የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሀገሪቱ ህገመንግሥትና ሌሎች የሀገሪቱ የምርጫ ህጎች በሚያዝዙት መንገድ ባለመካሄዱ የምርጫ ውጤቱ ተሽሯል። ሁለተኛ፣ የምርጫው ውጤት በዚህ አዋጅ በመሻሩ “ተመራጭ ፕሬዚዳንት” ተብሎ የታወጀው በይፋ እንዲነሳ ተወስኗል። ሦስተኛ፣ የሀገሪቱ ህገመንግሥት አንቀፅ 143 ና የሀገሪቱ ምርጫ ህግ በሚያዝዙት መሠረት የመጀመሪያው ተከሳሽ በ60 ቀናት ውስጥ አዲስ ምርጫ በጥንቃቄና ሂደቱ ሊረጋገጥ በሚቻልበት መንገድ እንዲያካሂድ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። የምርጫውን ማካሄጃ ወጭ በተመለከተ እያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ የራሱን ወጭ የሚሸፍንበትን መንገድ ይፈልግ” ብለዋል ዳኛው።

ዳኛው ማራጋ አክለው ስለዛሬው ውሣኔ የኬንያ ህግ በሚያዝዘው መሠረት ሙሉ መረጃ በ21 ቀናት ውስጥ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

ነኀሴ 2 ተካሂዶ የነበረው የኬንያ ምርጫ በተለይ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ድምፅ ቆጠራና ውጤቱንም ይፋ የማድረጉ አሠራርና ሂደት ተቃውሞ ገጥሞት የነበረ ሲሆን የኡሁሩ ኬንያታ ተቀናቃኝ የሆኑት ራይላ ኦዲንጋ የፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ውጤት እየተገለፀ በነበረ ጊዜ በሃገሪቱ ዋና የምርጫ ማዕከል እየተላለፉ የነበሩት ውጤቶች ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ካሉት ውጤቶች ጋር እየተስተያዩ አልነበረም ሲሉ ቅሬታ አሰምተው ነበር።

ሚስተር ኦዲንጋ የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ዛሬ ውሣኔውን ከሰጠ በኋላ ባደረጉት ንግግር “ዛሬ በአፍሪካ ታላቅ ፍትኅ ተፈፀመ” ብለዋል።

ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ
ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ

​“ዛሬ በአፍሪካ ዴሞክራሲ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት ፍትሃዊ ያልነበረን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት እንዲሻር ወስኗል። ይህ ውሣኔ በጣም ታሪካዊ ነው። ይህንን ፍትሃዊ ብያኔ ለኬንያ ህዝብ የሠጡትን ዳኞች በጣም ላመሰግን እወዳለሁ። የህግ ጠበቆቻችንንና መረጃ በመሰብሰብ የተባበሩትን የኬንያ ወጣቶችንም በዚህ አጋጣሚ በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ። እኛ በምርጫ ቦርዱ ላይ አሁን ባለበት አቋሙ ምንም እምነት የለንም። እንዲያውም ብዙዎቹ ከፍተኛ ወንጀል ስለፈፅሙ በህግ ሊጠየቁ ይገባል እንላለን። ስለዚህ እነዚህ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ህግ ፊት ቀርበው በኬንያ ህዝብ ላይ ለፈፀሙት አስፀያፊ ተግባር እንዲከሰሱ እንጠይቃለን” ብለዋል።

የኬንያ የምርጫ ቦርድ ተቀማጩ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ሙይጋይ ኬንያታ “8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል” ብሎ ውጤቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የኬንያታ ዋና ተቀናቃኝ የሆኑት “ራይላ አሞሎ ኦዲንጋ ያገኙት ድምፅ 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን በመሆኑ ተሸንፈዋል” ተብሎ ቢታወጅም ኦዲንጋ ውጤቱን ባለመቀበል አቤቱታቸውን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት ሄደዋል።

Kenya Election Results
Kenya Election Results

ፕሬዚደንቱ ኡሁሩ ኬንያታ የዛሬውን የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ከሰሙ በኋላ ውሣኔውን በግል ቢቃወሙም ለመቀበል ግን ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

“ዛሬ በተሰጠው ውሳኔ በግሌ አልስማማም፤ ግን አከብረዋለሁ። ፍርድ ቤት የራሱን ውሣኔ አሳልፏል፤ ማክበር አለብን። በተጨማሪም ኬንያዊያን አሁንም ደግሜ በሰላም እንድትነጋገሩ እጠይቃችኋለሁ። እናንተ ዘንድ አንዳች ጥፋት የለም። ስለዚህ ጎረቤቶቻችሁ ሁሌም ጎረቤቶቻችሁ ናቸው። ሁሌም የሚያስፈልጓችሁ ሰዎች ቢኖሩ እነርሱ ናቸው። እኔና የኔ ምክትል ወደ ህዝብ ተመልሰን ለመወዳደር ዝግጁ ነን” ብለዋል ኦዲንጋ።

ከፍርድ ቤቱ ውሣኔ በኋላ ብዙ የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊዎች ኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ወጥተው ደስታቸውን ሲገልፁ ተስተውለዋል። የኬንያ የምርጫ ሕግ በድጋሚ መደረግ ያለበት ምርጫ በ60 ቀናት ውስጥ መከወን እንዳለበት ይደነግጋል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የኬንያ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት ውድቅ ተደረገ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:58 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG