በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሜሎኒ የአፍሪካ ልማት እቅዳቸውን ይፋ አደረጉ


የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት አኪኑሚ አዴሲና ሮም፣ ጣሊያን እአአ ጥር 29/2024
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት አኪኑሚ አዴሲና ሮም፣ ጣሊያን እአአ ጥር 29/2024

የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚንስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ወደ አውሮፓ የሚፈልሱ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ፣ የኃይል ምንጭ አማራጮችን ለማበራከትና እንዲሁም በአውሮፓ እና በአፍሪካ መካከል የተማከለ አዲስ ግንኙነት ለመፍጠር በአገራቸው የተወጠነውን ግዙፍ የልማት እቅድ ከአሕጉሪቱ መሪዎች ጋር ባካሄዱት ጉባኤ ይፋ አደርገዋል። ሜሎኒ ጉባኤውን ‘የመጀመሪያው የተሳካ እርምጃ’ ብለውታል።

ሜሎኒ አክለውም የመንግስታዊው የነዳጅ እና ጋዝ ኩባንያ ‘ኢኒ’ መስራች በሆኑት ኤንሪኮ ማቲ ስም የተሰየመውን ይህን የአገራቸውን እቅድ ‘ከአፍሪካ ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን ከኃይል አቅርቦት ባለፈ ስትራቴጂያዊ አጋርነትን በማጎልበት ላይ ያተኮረ፣ ከአዲስ አስተሳሰብ ወይም ፍልስፍና የሚቆጠር ነው’ ብለውታል።

ዋና ዋና የአውሮፓ ሕብረት እና የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣናትም የ5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዩሮ ወይም የ5 ነጥብ 95 ቢሊዮን ዶላር የማስጀመሪያ ወጭ የተመደበለትን የጣሊያኑን ዕቅድ ‘በአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች ለመታደግ ለተወጠኑ እና በንጹህ የኃይል ልማት ላይ ላተኮሩት ጅምሮች አጋዥ ይሆናል’ ሲሉ አወድሰውታል።

‘የአፍሪካ ሃገራት አስቀድመው ምክር ቢጠየቁ ይመርጡ እንደነበር’ ያመለከተው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በበኩሉ፤ እውን የማይደረጉ ተጨማሪ ባዶ ቃል ኪዳኖችን መስማት እንደማይሻ ለጉባኤው በመግለጽ፡ ጥንቃቄ የተመላበት አቀራረብ መከተል መርጧል።

ከአፍሪካ መሪዎች ጋር አለመምከራቸውን አስመልክቶ በጉባኤው መዝጊያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የተጠየቁት ሜሎኒ በሙከራ ፕሮጄክቶች ስለሚተገበሩ የተለዩ ሃሳቦች በመክፈቻ ንግግራቸው በማንሳታቸው “ሳላሳስት አልቀረሁም” ሲሉ የቀረበውን አስተያየት መቀበላቸውን አመልክተዋል። ሆኖም ጉባኤው ‘በተጨባጭ ምሳሌዎች የተደገፈ ንድፍ በማሰናዳት አገራቸው የያዘችውንና በትብብር ተግባራዊ ሊሆን የሚችል አዲስ የግንኙነት ፍልስፍና ለአፍሪካ መሪዎች አሳይቷል’ ብለዋል። "ጉባዔው ስትራቴጂውን ማጋራት ብቻ ሳይሆን፤ በአጭሩም ቢሆን የፕሮጀክቱን የመጨረሻ ፋይዳ ለማመላከት መሰረታዊ እርምጃ ነበር" ሲሉም አብራርተዋል።

ጣሊያን የሰባቱን የዓለም ባለጸጋ አገሮች ቡድን የፕሬዝዳንትነት መንበር ከተረከበች ወዲህ የመጀመሪያው ትልቁ መድረክ በሆነው የሮሙ ጉባኤ ከሃያ በላይ የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ የአውሮፓ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ እንዲሁም የአለም አቀፍ አበዳሪ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG