በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢራንና የሳዑዲ መፋጠጥና የአካባቢው ሁኔታ


በሳዑዲ አረቢያና በኢራን መካከል የተካረረው ውዝግብ የፖለቲካ እንጂ የዕምነት ጉዳይ አይደለም ሲሉ ሁለት ምሁራን ለቪኦኤ ገልፀዋል። ማረሚያ፡- በቀደመ ዘገባ "ሱዳን የሳዑዲ አረቢያን አምባሣደር አባርራለች" የተባለው፤ "የኢራንን አምባሣደር አባርራለች" በሚል እንዲታረም ከይቅርታ ጋር እናሳስባለን፡፡

የሳዑዲ አረቢያና የኢራን ግንኙነት ከድጡ ወደማጡ እያዘገመ መሆኑን የሚያሳዩ አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ መሆናቸውን ዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ናቸው።

ሳዑዲ አረቢያ ለፖለቲካና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ለጩኸትና ለሰላማዊ እምቢታ ሲታገሉ እንደነበረ ሌሎች የሚናገሩላቸውን፤ ሪያድ ግን “ለአመፅ ያነሣሳ፣ የውጭ ጣልቃገብነትን የጋበዘና ብረት የጨበጠ ወንጀለኛ ነበር” የምትላቸውን ሺአ የእምነት መሪ ሼህ ኒምር አል-ኒምርን በሞት ከቀጣች ወዲህ የተነሣ መካረር ነው ሁለቱን ሃገሮች ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶቻቸውን እስከማቋረጥ ያደረሣቸው።

በሼህ አል-ኒምር ላይ በጥቅምት 2007 ዓ.ም የሞት ፍርድ ሲጣልባቸው ኢራን ፍርዱ ተፈፃሚ እንዳይደረግ በብርቱ አስጠንቅቃ ነበር። ሳዑዲ አረቢያ “የምትከፍለው ዋጋ ውድ ይሆናል” ሲልም የኢራን ጦር ዝቶ ነበር።

የተፈረደው ተፈፀመና ጦሱ ለሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት መሻከር ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የአካባቢውን ሃገሮች በ“የቡድንና የቡድን አባቶች” ጎራ አሰልፏል።

ባሕሬንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ከቴህራን ጋር ያላቸውን ግንኙነት አንዷ በጥሣለች፤ ሌላዋ አላልታለች።

ሱዳን የኢራንን አምባሣደርና ሙሉውን ዲፕሎማሲያዊ ሚሲዮን ከኻርቱም አባርራለች፤ የራሷንም ከቴህራን አውጥታለች፡፡

“ሁለቱ ሃገሮች ወትሮም የመን፣ ሦሪያና ኢራቅ ውስጥ ባሉ አለመግባባትና ትርምሾች ውስጥ በየአንፃር ጎራ ቆመው በእጅ አዙር ይቆራቆሳሉ” እየተባለ ይነገርባቸዋል።

ለመሆኑ ይህ የኢራንና የሳዑዲ ዐረቢያ፤ የሱኒና የሺአ ፀብ ምንድነው? የሁለቱ ሃገሮች መፋጠጥና መካረር የሚፈጥረው የአካባቢው መልክዓ-ምድራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ምን ይመስል ይሆን? በዚህ መፋጠጥ ውስጥ የኢትዮጵያስ አቋምና መዘዝ ምን ሊሆን ይችላል?

ከአዲስ አበባ የእሥልምና አጥኝና ተመራማሪ፤ እንዲሁም በርካታ መፅሐፍትን የፃፉት ኡስታዝ ሃሰን ታጁ፤ ከዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ በቴክሣስ ጠቅላይ ግዛት በኮሊን ኮሌጅ የሥነ-ምጣኔኃብር ፕሮፌሰር መሐመድ አባጀበል ጣሂሮ ለቪኦኤ አድማጮች ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል።

ዘገባውንና ቃለ-ምልልሶቹን ከያዙት ፋይሎች ሙሉውን መረጃ ያገኛሉ።

የኢራንና የሳዑዲ መፋጠጥና የአካባቢው ሁኔታ
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:17 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG