ሙላቱ አስታጥቄ በ1950ዎቹ ወደ ብርታንያ ያመራው ኢንጂኔሪንግ ለመማር ነበር። የሙዚቃ ፍቅሩ አይሎበት፤ የምት መሳሪያዎችና ዛይለፎን ተማረ።
ኢትዮ ጃዝ የተፈጠረው በሙላቱ አስታጥቄ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ሙላቱ አስታጥቄ የተወለደው ጅማ ነው። ብሪታንያ ትሪኒቲ ኮሌጅ እና ዩናይትድ ስቴትስ ቦስተን በሚገኘው በርክሌ ዩኒቨርስቲ የምዕራባውያኑን ሙዚቃ ተምሯል። ኢትዮጵያዊ ዜማዎችን ከምዕራባውያኑ ጃዝ የሙዚቃ ስልት ጋር በመደባለቅ ከሀገር ባለፈ የምዕራባውያኑን ቀልብ የገዛ ሙዚቀኛ ነው።
“የምዕራባውያኑን በአስራሁለት ድምፅ ላይ የተመሰረተውን የሙዚቃ ስልት በአምስት ድምጽ በተመሰርተው ከኛ ሙዚቃ ጋር ሲደባለቅ በጥናት በምርምር ሁለቱን በማዋሃድ ካልተደረገ በስተቀር የኛ ቅኝትን ሊደመስሰውና ውበቱን በቀላሉ ሊያሳጣው ይችላል።”
ሄኖክ ተመስገን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቅዱስ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት መምህርና በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር መድረኮች ላይ ቤዝ ጊታር በመጫወት ይታወቃል። ሄኖክ በዩናይትድ ስቴትስ በርክሌ የሙዚቃ ኮሌጅ ሙዚቃን አጥንቷል። በአዲስ አበባ በሚገኘው በመካኒሳ የጃዝ ት/ቤት መምህር ነው። በአሁኑ ጊዜ በርካታ ወጣት ሙዚቀኞችን በማስተማር ላይ ይገኛል።
“በአለም ላይ ከየትም ሃገር የመጣ ሙዚቃ መልካሙን ወስዶ ከራሱ ሃገር ጋር ወይም ከሌላ ሃገር ጋር ቀያይጦ እንደፈለገው ጥናትን አድርጎ ለጆሮ ጥሩ የሆነ ዜማና ሰው ልብ የሚነካ ሙዚቃ እስከሰራ ድረስ፤ የራስን እንዳለ ጠብቆ ከሌሎች ጋር ምርምር ማድረግ ለሙዚቃ እድገት ለማንም ሃገር ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ” ይላል ሔኖክ ተመስገን።