በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኤችአር 128 ለድምፅ ተቀጠረ


ኢትዮጵያ ውስጥ መብቶች መከበርና አካታች ወይም አሳታፊ የሆነ አስተዳደርን ለማበረታታት በሚል የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ደረጃዎች ሲመክርበት የቆየው ኤችአር 128 የውሣኔ ረቂቅ ለፊታችን ሚያዝያ ድምጭ ሊሰጥበት ተቀጥሯል፡፡

“ኢትዮጵያ ውስጥ ለመብቶች መከበርና አካታች ወይም አሳታፊ የሆነ አስተዳደርን ለማበረታታት” በሚል የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት በተለያዩ ደረጃዎች ሲመክርበት የቆየው ኤችአር 128 የውሣኔ ረቂቅ ለፊታችን ሚያዝያ ድምፅ ሊሰጥበት ተቀጥሯል፡፡

ይህ ባለፈው የካቲት 8/2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ለ115ኛው የዩናይትድ ስቴትስ የተወካዮች ምክር ቤት በኒው ጀርሲው ሪፐብሊካን እንደራሴ ክሪስ ሄንሪ ስሚዝ የቀረበ ረቂቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ‘በመንግሥቱ እየተፈፀሙ ናቸው’ የሚባሉ በሰብዓዊ መብቶች ረገጣና በማዋከብ እርምጃነት የተፈረጁ ዝርዝር ማስረጃዎችን የያዘ ነው፡፡

ኮንግረስማን ክሪስ ስሚዝ
ኮንግረስማን ክሪስ ስሚዝ

ማስረጃዎቹ ‘በየአደባባዩ በመንግሥት ኃይሎች ተፈፅመዋል’ የተባሉ ግድያዎችንና እሥራቶችን፣ የተያዙ ሰዎችን የፖለቲካና የአስተሳሰብ መሪዎችን ስሞች፣ ‘ለአፈና ጉዳይ ወጥተዋል’ የተባሉ ሕጎችን፣ ቀደም ሲል ተጥሎ የነበረን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ሌሎችም የመንግሥት አድራጎቶችን የሚጠቅስ ሲሆን አንዳንዶቹ እንዲያውም “የጦር ወንጀልና በሰብዕና ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎችን እንደሚተካከሉ” አመልክቷል፡፡

ምንም እንኳ በኤችአር 128 ውስጥ በተዘረዘሩት ክሦች ላይ ተዓማኒነት ያለው ገለልተኛ ምርመራ አለመደረጉንና ለሚባሉት ጥፋቶች ‘ተጠያቂ ነው’ የሚባል ሰው አለመያዙን ረቂቅ ሰነዱ ቢጠቁምም “የተወካዮች ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅመው በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ የፈፀሙትን ግድያ ያወግዛል” ሲል አስፍሯል።

በሰላማዊ ተቃውሞ የመሰብሰብና የመናገር ሕገመንግሥታዊ መብቶቻቸውን ስለተጠቀሙ ጋዜጠኞች፣ ተማሪዎች፣ የመብቶች ተሟጋቾች፣ የፖለቲካ መሪዎች ተይዘው መታሠራቸውን፣ ፀረ-ሽብር ሕጉም የፖለቲካና ሲቪል ተቃውሞዎችን፣ እንዲሁም የጋዜጠኛነት ነፃነቶችን ለማፈን ጉዳይ መዋሉን እንደሚያወግዝ ይናገራል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ተቃዋሚዎችም ከሁከት እንዲቆጠቡ፣ እንዲሁም በሰልፎች ወቅት ሁከት እንዲቀሰቀስ ከማበረታታት እንዲታቀቡ ጥሪ ያስተላልፋል።

ይህ ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ ሰነድ በምክር ቤቱ የተለያዩ ኮሚቴዎች እየተመከረበት ባለበት ጊዜ ኢትዮጽያ ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካና በረቂቅ ሰነዱ ላይ ከሠፈሩ ክሦች ጋር የተያያዙ ለውጦች እየተደረጉ ቢሆንም ምክር ቤቱ ሰሞኑንም ተጨማሪ እማኝነቶችን ሲሰማ ከቆየ በኋላ በሙሉው የተወካዮች ምክር ቤቱ ጉባዔ ድምፅ እንዲሰጥበት መቀጠሩን ከሰነዱ አርቃቂና አቅራቢዎች አንዱ የሆኑት የኮሎራዶው ሪፐብሊካን እንደራሴ ማይክል ሃዋርድ ኮፍማን አድንቀዋል።

ኮንግረስማን ማይክ ኮፍማን
ኮንግረስማን ማይክ ኮፍማን

“የተወካዮች ምክር ቤቱ በኤችአር 128 ላይ ድምፅ እንደሚሰጥ ማስታወቁ በጉዳዩ ውስጥ የተሣተፉ ሁሉ ቁጥራቸው ለበዛ ሰዓቶች ሲያደርጉ ለቆዩት ጠንካራ ሥራ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጡ ለተያዘው የማይናወጥ ትግል እማኝነት የሚቆም ነው” ብለዋል ኮፍማን።

የድምፅ ቀጠሮው “ትክክለኛውን ተግባር ለመፈፀም እየተካሄደ ባለው ትግል ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት በመቶ ሺኾች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ማፍሰሱ እርባና ቢስ መሆኑንም አረጋግጧል” ብለዋል አክለው።

የተወካዮች ምክር ቤቱ አብዝኀ እንደራሴዎች መሪ ኬቭን ማካርቲ ረቂቁን ለተወካዮች ምክር ቤቱ ድምፅ ለማቅረብ በመወሰናቸውም በኢትዮጵያም አሜሪካም ውስጥ “ምሥጋናቸውን እያቀረቡላቸው ካሉ ብዙ ድምፆች ጋር እንደሚቀላቀሉ” ሚስተር ማይክል ኮፍማን አመልክተዋል።

ይህንን ባለፈው ሐምሌ 2009 ዓ.ም. በተወካዮች ምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ ያለፈ ኤችአር 128 ረቂቅ በብርቱ ከሚደግፉ የዩናይትድ ስቴትስ እንደራሴዎች ኮፍማን አንዱ ሲሆኑ የካሊፎርንያዋ ዴሞክራቲክ እንደራሴ ካረን ሩዝ ባስ፣ የኢሊኖይ ዴሞክራት ኬሊ በርክ፣ የቴክሳሱ ዴሞክራት ማርክ ቪሲ፣ የሚኔሶታው ዴሞክራት የተወካዮች ምክር ቤት አባል ኪት ኤሊሰንም የረቂቁ ስፖንሰሮች ናቸው።

የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

ኤችአር 128 ለድምፅ ተቀጠረ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:25 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG