በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሐረር ውኃ “በአንድ ሣምንት ውስጥ ታገኛለች” - የሐረሪ ባለሥልጣን


የኢፋባቴ የውኃ ማምረቻና ማሠራጫ
የኢፋባቴ የውኃ ማምረቻና ማሠራጫ

ለሐረር ከተማ ይደርስ የነበረው የውኃ አቅርቦት የሁለት ማምረቻና ማከፋፈያዎች ሥራና አቅርቦት በአካባቢዎቹ የሚገኙ ናቸው በተባሉ ሰዎች ከተስተጓጎሉ በኋላ በተደረጉ የተለያዩ ጥረቶች “በአንድ ሣምንት ጊዜ ውስጥ መፍትኄ ይገኛል” ሲሉ የሐረሪ ክልል የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አስታውቀዋል።

ለሐረር ከተማ ይደርስ የነበረው የውኃ አቅርቦት የሁለት ማምረቻና ማከፋፈያዎች ሥራና አቅርቦት በአካባቢዎቹ የሚገኙ ናቸው በተባሉ ሰዎች ከተስተጓጎሉ በኋላ በተደረጉ የተለያዩ ጥረቶች “በአንድ ሣምንት ጊዜ ውስጥ መፍትኄ ይገኛል” ሲሉ የሐረሪ ክልል የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ አስታውቀዋል።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ከቪኦኤ ጋር ዛሬ ባደረጉት ቃለ-ምልልስ የሃረማያ-ኢፋባቴን ማምረቻ “አሥር ሚሊየን ብር በአምስት ቀናት ውስጥ ይሰጠን” ብለው በመያዣነት ካገቱ ሰዎች የተወሰኑት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንና ሕግ ፊት እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ኤረር አካባቢ የሚገኘው ማምረቻ ከልማት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ባነሱ የአካባቢው ነዋሪዎች መስተጓጎሉን ውኃ የማስተላለፊያው መሥመር በየቦታው መሰበሩንና መጎዳቱን አቶ ተወለዳ ገልፀዋል።

ከየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ መሆናቸውንና ዘላቂና የጋር መፍትኄ ለማግኘት ዙሪያውን ያሉ የኦሮምያና የሐረሪ ባለሥልጣናትና መሥሪያ ቤቶች፣ መንግሥቱና ኅብረተሰቡ በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ተወለዳ የመብትና የልማት ጥያቄዎች መነሣታቸው ትክክል ነው ብለው እንደሚያምኑ ነገር ግን ጥያቄዎቹ የሕግ የበላይነትና አግባብን በጠበቁ መንገዶች ቢቀርቡ ይበልጥ ተደማጭነት እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

ይህ ለስድስት ወራት ያህል ብልጭ ድርግም ሲል የቆየና በመጨረሻዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ከተማዪቱን ውኃ ጨርሶ ያሳጣ ችግር ተቃልሎ አሁን የተያዙት የቴክኒክና የጥገና ሥራዎች ሲጠናቀቁ “ሐረር ከችግሩ በፊት ወደነበረችበት የፈረቃ ውኃ አቅርቦት ትመለሣለች” ብለዋል የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጁ አቶ ተወለዳ አብዶሽ።

በውኃ አቅርቦቱ መስተጓጎል የተጎዳው የሐረር ከተማ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ሃረማያን፣ አወዳይንና ማምረቻዎቹ ያሉባቸውን ማኅበረሰቦች ጨምሮ ስፋት ያለው አካባቢ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል።

ሙሉውን ቃለ-ምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG