የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ያፀደቀው በክልል የመደራጀት ውሳኔ በመንግሥት ምላሽ እስኪሰጥበት ድረስ ሕዝቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ ዋና አስተዳዳሪው አቶ መሐመድ ጀማል ጠየቁ።
አስተዳዳሪው ጥሪውን ያቀረቡት የጉራጌ ዞን ከሌሎች ዞኖች ጋር በመሆን ክልል እንዲመሠርት በመንግሥት የቀረበው ሐሳብ በዞኑ ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።
የአካባቢውን ፀጥታና ደኅንነት እየቃኘ የሚገኘው ኮማንድ ፖስት ደግሞ “የምክር ቤቱን ውሳኔ መነሻ አድርገው ሁከትና ብጥብጥ በሚፈጥሩ አካለት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ” አስጠንቅቋል።
በመንግሥት የቀረበው ሃሳብ የጉራጌ፣ የሃድያ፣ የስልጢ፣ የሃላባና የከምባታ-ጠምባሮ ዞኖች እንዲሁም የየም ልዩ ወረዳ አንድ ክልል እንዲመሠርቱ የሚጠይቅ ነው። ይህ የመንግሥት ሃሳብ ግን አብዛኛዎቹ የራሱ የገዥው ፓርቲ ተመራጮች በሆኑ 52 የምክር ቤት አባላት ተቃውሞና በ40 ድጋፍ ውድቅ ተደርጓል።
ተቃውሞ ያስመዘገቡት የምክር ቤት አባላት የጉራጌ ዞን ከሌሎች ጋር በመሆን ሳይሆን ብቻውን ክልል እንዲመሠርት የሚፈልጉ ናቸው።
በመንግሥት የቀረበውን ሃሳብ የተቃወሙና የደገፉ የጉራጌ ዞን ምክር ቤት አባላትን አስተያየቶች ያካተተው ዘገባ ዝርዝሩን ይዟል፤ ያዳምጡት።