በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ታዋቂው ጄኔቲሲስት ገቢሳ ኢጂታ የአሜሪካ ብሔራዊ የሳይንስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ኾኑ


ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካዊ ገቢሳ ኢጄታ ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እጅ፣ ትላንት ማክሰኞ ሜዳሊያቸውን ሲቀበሉ
ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካዊ ገቢሳ ኢጄታ ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እጅ፣ ትላንት ማክሰኞ ሜዳሊያቸውን ሲቀበሉ

ጄኔቲሲስቱ ትውልደ ኢትዮጵያ አሜሪካዊ ገቢሳ ኢጄታ፣ የአሜሪካ ብሔራዊ የሳይንስ ሜዳሊያ ተሸላሚ በመኾን፣ ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እጅ፣ ትላንት ማክሰኞ ሜዳሊያቸውን ተቀብለዋል።

ገቢሳ ኢጄታ፣ በዕፀዋት ማዳቀል የዘረመል ወይም ጄኔቲክስ ሳይንስ እና በዓለም አቀፍ ግብርና መስክ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት፣ በአሜሪካ የፐርዱ ዩኒቨርሲቲ፣ የዓለም አቀፍ የምግብ ዋስትና ማዕከል ዋና ዲሬክተር የኾኑት ፕሮፌሰሩ፣ የዩኒቨርስቲው የምግብ ዋስትና እና ዘላቂ ልማት ፕሬዚዳንታዊ አባልም ናቸው።

ሽልማቱ፣ በሳይንስ መስክ የሚሰጥ ከፍተኛው ሜዳሊያ ነው፤ ተብሏል።

ትናንት በዋይት ሃውስ በነበረው ስነ ሥርዓት ላይ 9 ሰዎች በሳይንስ መስክ ተሸላሚ ሲሆኑ፣ 11 ሰዎች ደግሞ በቴክኖሎጂ እና በፈጠራ መስክ ተሸላሚ ሆነዋል።

ገቢሳ ኢጄታ፣ ለሰው እና ለእንስሳት በምግብነት በሚያገለግለው ማሽላ ላይ ከፍተኛ ምርምር በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ እ.አ.አ በ2009፣ ድርቅንና አረምን መቋቋም የሚችል የማሽላ ዝርያ በማግኘት ለምግብ ዋስትና ላበረከቱት አስተዋፅኦ፣ የዓለም ምግብ ሽልማት አሸናፊ ኾነዋል።

በምርምር ውጤታቸው ምክንያት፣ የማሽላ ምርት በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ፣ ከሰሃራ ግርጌ ባሉ ሀገራት የሚኖሩ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን መመገብ አስችሏል፤ ተብሏል።

ፕሮፌሰር ገቢሳ ኢጄታ፣ በኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት፣ በሐሮማያ እና በጂማ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት እና በተመራማሪነት አገልግለዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG