በጋምቤላ ክልል ከሚስተዋለው የጸጥታ ችግር ጋራ በተያያዘ፣ “በመንግሥትም ኾነ በፓርቲ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በአግባቡ አልፈጸሙም፤” ያላቸውን አራት ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነት ማንሣቱን፣ የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡
የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት፣ ትላንት ሰኞ፣ መጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በክልሉ ከሚታየው የጸጥታ መደፍረስ ጋራ በተያያዘ፣ "ኃላፊነታቸውን አልተወጡም፤ ተልእኳቸውንም አልፈጸሙም፤" በሚል የገመገማቸውን አራት ከፍተኛ አመራሮች ከሥልጣን ማንሣቱን አስታውቋል፡፡
መግለጫው እንደሚያሳየው፣ ከኃላፊነታቸው የተነሡት አመራሮች፦ የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ አኳይ ኡቡቲ፣ የሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ቾል ኩን፣ የክልሉ የገጠር መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዲሬክተር አቶ ቢተው ዳክ እና የኑዌር ብሔረሰብ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቡኝ ኒያል ናቸው፡፡
ከተነሡት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊው አቶ ቾል ኩን፣ ባለፈው ሳምንት ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ክልላዊ መንግሥቱ፥ የብሔር ግጭቶችን ቀስቅሰዋል፤ በድርጊቱም ተሳትፈዋል፤ በተባሉ የጸጥታ መዋቅር አባላት ላይ ርምጃ እየወሰደ እንደኾነ ገልጸው ነበር፡፡
እየተወሰደ ነው ስለተባለው ርምጃ፣ የክልሉ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ኡጁሉ ጊሎ፣ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡን ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ “ከጸጥታ ጋራ በተያያዘ፣ የመጨረሻው ሪፖርት ከክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ አልደረሰንም፤” የሚል አጭር የጽሑፍ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
ቀደም ሲል የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት፣ ባወጣው ሌላ መግለጫም፣ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በክልሉ፥ የብሔር ግጭት፣ ሽብርተኝነት፣ ደረቅ ወንጀሎች እና ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን የመሳሰሉ ችግሮች እየጨመሩ መምጣታቸውን አስታውቋል፡፡ እኒኽም ችግሮች፣ በክልሉ ግጭቶች እንዲባባሱ ማድረጋቸውን አስረድቷል፡፡
መግለጫው አያይዞም፣ አሁን የሚታየው የብሔር ጽንፈኝነት እና ፖለቲካዊ ችግር ዋና ተሸካሚ አመራሩ እንደኾነ አስገንዝቦ፣ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች እና ከውጪ የሚዘወሩ ያላቸው የማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛዎችም ሚና እንዳላቸው አመልክቷል፡፡ ከመካከላቸው፣ ሥልጣንን በሕገ ወጥ መንገድ ለመያዝ የሚጥሩ አካላት መኖራቸውንም ጠቅሶ፣ “በእነዚኽ አካላት ላይ ርምጃ እወስዳለኹ፤” ሲልም አስጠንቅቆ ነበር፡፡
ርምጃው፣ በፀጥታ መዋቅር አባላት ላይ ተጀምሮ እንደነበረ ያስታወቀው መግለጫው፣ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ወንጀሎች የተሳተፉ ሰዎችም ጭምር በቁጥጥር ሥር ውለው እንዲጠየቁ የማድረግ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቷል፡፡
በጋምቤላ ክልል፣ በቅርቡ፣ በአንድ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ታጣቂዎች ፈጸሙት በተባለ ጥቃት፣ አምስት መንገደኞች መገደላቸውንና 36 ሰዎች መቁሰላቸውን፣ የአሜሪካ ድምፅ፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች እና የጋምቤላ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ዋቢ አድርጎ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የክልሉ መንግሥትም፣ በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፈና አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጦ፣ ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ እንደኾነ ገልጾ ነበር፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።
መድረክ / ፎረም