በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያሏት ስጋቶች


አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያሏት ስጋቶች
please wait

No media source currently available

0:00 0:14:44 0:00

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያሏት ስጋቶች

በዩናይትድ ስቴትስ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ፣ የአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት የሚከተለውን ፖሊስ አስመልክቶ፣ የምስክርነት ቃል አዳምጧል። በምክርቤቱ ተገኝተው ቃላቸውን የሰጡት የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር እና በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት /ዩኤስኤድ/ የአፍሪካ ቢሮ ምክትል ረዳት አስተዳደር ታይለር ቤክልማን ሲሆኑ በኢትዮጵያ በሚታየው የፖለቲካ፣ የደህነንት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አሜሪካ ያላትን አቋም አብራርተዋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ውስጥ የተካሄደውን የእማኞችን ቃል የማዳመጥ ሂደት በንግግር የከፈቱት፣ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ፣ የአፍሪካ ንዑስ ኮሜቴ ሊቀመንበር የሆኑት እንደራሴ ጆን ጄምስ ናቸው።

ኮሚቴው በዋናነት ከአንድ አመት በፊት በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ትግበራን ለመፈተሽ እና በተለይ ደግሞ የአሜሪካ እና ኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለመፈተሽ የተሰበሰበ መሆኑን ያብራሩት ጄምስ ኢትዮጵያ እየተጓዘችበት ያለው መንገድ እና አሜሪካ የምትከተለው የፖሊሲ አቅጣጫ እንደሚያሳስባቸው ገልፀዋል።

የምስክርነት ቃላቸው እንዲሰጡ የተጠሩት የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር እና በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት /ዩኤስኤድ/ የአፍሪካ ቢሮ ምክትል ረዳት አስተዳደር ታይለር ቤክልማንም፣ ስለ ሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት አፈፃፀም፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ስለቀጠለው ግጭት እና ኢትዮጵያ እንደ ቻይና እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ የመሳሰሉ ሀገሮች ጋር ስለፈጠረችው ሰፊ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲያብራሩ ጠይቀዋቸዋል።

አስቀድመው የምስክርነት ቃላቸውን የሰጡት አምባሳደር ማይክ ሐመር "ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ከፍተኛ መሻሻል አይተናል። የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር እና ሌሎች ገለልተኛ ታዛቢዎች እንዳስታወቁት፣ የሰሜኑ ጦርነት ከቆመ በኃላ በትግራይ ውስጥ ይፈፀም የነበረው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ጥሰት በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። ጎን ለጎን ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ያቋቋመው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መርማሪ ኮሚሽን ሪፖርት፣ አሁንም በምዕራብ ትግራይ ችግር መኖሩን እና በኤርትራ ኃይሎች እየደረሰ ያለው በደል አሁንም መቀጠሉን ማመልከቱ ብዙ መሰራት እንዳለበት ያሳያል" በማለት የባይደን እና ሃሪስ መንግስት በዋናነት በሰላም ስምምነት አፈፃፀም ላይ እንዳተኮረ ገልፀዋል።

አምባሳደር ሐመር አያይዘው በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል የቀጠለው ግጭትም የአሜሪካን አስተዳደር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው አመልክተዋል።

"ከግጭቱ ጋር የተያያዘ መጠነ ሰፊ እና ከባድ ፆታዊ ጥቃት፣ በጣም ብዙ ቁጥር ያለው ሰው ህይወት መጥፋት እና ከፍተኛ መጠን ያለው የኢኮኖሚ መቃወስን ጨምሮ፣ ከፍተኛ ጥቃት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን የሚያሳዩ ተዓማኒነት ያላቸው ሪፖርቶች አሉ። በቅርቡ በአማራ ክልል በአስቸኳይ አዋጁ ስር እየተፈፀሙ ያሉ የንፁሃን ሰዎች ሞት፣ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ እስር፣ እና በዘፈቀደ የሚፈፀም ግድያ ዙሪያ የሚወጡ ሪፖርቶች ያሳስቡናል። በዚህ ግጭት ውስጥ ያሉ አካላት ሁከትን ከሚፈጥሩ የጥላቻ ንግግሮች እንዲቆጠቡ እና የሰላማዊ ዜጎችን ደህንነት እንዲጠብቁ አሳስበናል።"

አምባሳደር ሐመር አክለው የኢትዮጵያ መንግስት በአማራ ክልል ላይ የጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያነሳ፣ ኢንተርኔት እንዲለቀቅ እና መገናኛ ግዙሃን ወደ ክልሉ ገብተው ያለውን ሁኔታ እንዲያጣሩ እንዲፈቀድ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መነጋገራቸውን እና ማሳሰባቸውን ገልፀዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ስምምነት ለትግራይ ህዝብ ሲፈለግ የነበረውን እፎይታ መስጠቱን ያመለከቱት በዩኤስ ኤይድ የአፍሪካ ቢሮ ምክትል ረዳት አስተዳደር ታይለር ቤክልማንም፣ የስምምነቱ አካላት የሆኑ ትጥቅ ማስፈታት፣ የሰራዊት መበተን እና ከሰላማዊ ህዝብ ጋር ማዋሃድ እና የሽግግፍ ፍትህ የመሳሰሉ ስራዎች አሁንም እንደሚቀሩ አመልክተዋል።

"ኢትዮጵያ አሁንም የግጭቱ ውጤት ከሆኑ እንደ ሰፊ ፆታዊ ጥቃት እና እንደ አማራ እና ኦሮሚያ ክልል ባሉ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር ትግል ላይ ናት"

የምስክርነቱን ሂደት የመሩት ሊቀመንበሩ ጄምስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ለኢትዮጵያ የባህር በር መኖር አስፈላጊነትን አስመልክተው በቅርቡ አድርገውት የነበረው ንግግር ወደፊት በቀጠናው አዲስ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ፍራቻቸውን ገልፀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ፍላጎት የሌለው እንደሆነ እና ምዕራቡን አለም፣ በተለይም ዩናይትድ ስቴትስን የሚፈልገው እየተባባሰ የመጣውን የገንዝብ ችግሩን ለመፍታት ብቻ መሆኑ እያሳሰባቸው መሄዱን አብራርተውም ከምስክሮቹ ምላሽ ጠይቀዋል።

"እ.አ.አ በጥቅምት 2023፣ አብይ በአደባባይ፣ ኤርትራ ነፃ ከወጣች ጊዜ ወዲህ የባህር በር የሌላት ሀገር መሆኗን እና ህዝቧን ከጂኦግራፊያዊ እስር ቤት ለማውጣት የቀይ ባህር ወደብ ማግኘቷ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል። ታሪክን፣ በጂኦግራፊብ፣ በብሄርን እና በኢኮኖሚ ምክንያቶችን በመጥቀስ የቀይ ባህርን ጉዳይ መክፈት ወደፊት አዲስ ግጭት ሊቀሰቅስ የሚችል ጉዳይ ነው።"

አምባሳደር ሐመር ለዚህ ፍራቻ አዘል ጥያቄ ምላሽ የሰጡት፣ ስጋቱ የአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የሌሎች በቀጠናው የሚገኙ ሀገራትም ጭምር መሆኑን በማስመር ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዚህ ንግግራቸው ማስተባበያ መስጠታቸውንም ጠቅሰዋል።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልሰው ወደብ የማግኘት ጥረቱ በንግድ ትስስር እና በሰላማዊ መንገድ እንደሚደረግ በይፋ መናገራራቸውን ማመልከት እፈልጋለሁ። በእርግጠኝነት ቀጠናው የሚፈልገው የመጨረሻው ነገር ሌላ ጦርነት ነው። ከዚህ አንፃር በዩናይትድ ስቴትስ እይታ፣ በቀጠናውም ሆነ፣ በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶችን እና ጥቃቶችን ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት አስፈላጊ መሆኑን በግልፅ ነግረናቸዋል።"

ከግማሽ ሚሊየን በላይ የሚሆን ሰው ህይወት የጠፋበትን ሰሜናዊውን የኢትዮጵያ ክፍል መልሶ ለመገንባት ከ20 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ዩናይትድ ስቴትስ ግምት አስቀምጣለች። 28 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ብድር ያለባት ኢትዮጵያ ግን በከፍተኛ የዋጋ ንረት እና የውጭ ምንዛሬ እጥረት ኢኮኖሚዋ እየተንገዳገደ በመሆኑ እንደ ቻይና እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይ ኤም ኤፍ ከመሳሰሉ አበዳሪዎች የእፎይታ ጊዜ ጠይቃለች።

አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ይህ ድጋፍ ያስፈልጋታል ወይ ለሚለው የአሜሪካ ተመራጭ ምክርቤት አባላት ጥያቄ ቤክልማን "ኢትዮጵያ ውስጥ የኢኮኖሚ ውድቀት እንዳይከሰት መከላከል እና ኢትዮጵያውያን በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ ማገዝ፣ ለእኛም፣ ለኢትዮጵያ ህዝብም እንዲሁም ለዓለምም ይጠቅማል ብለን እናምናለን። ይህን የምናደርገው ከ126 ሚሊየን ህዝቡ ከ40 ከመቶ በላይ የሚሆነው አብዛኛው ከ15 አመት በታች የሆነ ወጣት ባለበት ሀገር ላይ ነው። ለዛ ነው እነዚህን ሂደቶች የምንደግፈው። ድጋፋችንን ስንሰጥ ግን ከእሴቶቻችን እና ኢትዮጵያ ውስጥ ካለን ጥቅም ጋር በሚስማማ መልኩ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በቅርብ ዓመታት ውስጥ፣ በኦሮሚያ ክልል በመቶ ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የኾነውን፣ በኢትዮጵያ መንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል የሚካሄድ ግጭት ለመፍታት በታንዛኒያ የተካሄዱ ድርድሮች ያለስምምነት ተጠናቀዋል። ይህም በክልሉ የሚፀሙ ግድያዎች እና የመብት ጥሰቶች እንዲቀጥሉ አድርጓል።

የአሜሪካ ምክርቤት ተመራጭ እንደራሴ ቶማስ ኪን፣ በድርድሮቹ ላይ አሜሪካን ወክለው ታዛቢ ለነበሩት እና እነዚህን ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የአሜሪካ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን ላሰመሩበት አምባሳደር ሐመር፣ ድርድሩ እንዳይሳካ እንቅፋት የሆነው ምን እንደሆነ እና ድርድሩ መቼ ሊቀጥል ይችላል ብለው እንደሚያምኑ ጥያቄ አቅርበውላቸዋል።

በምላሻቸውም " እኔ ይህን ኃላፊነት ሰኔ ላይ ስረከብ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው አስከፊ ጦርነት መቼም እንደማያበቃ ነበር የተነገረኝ። ሆኖም በፀጥታ ዲፕሎማሲ እና ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ለውጥ ያመጣ ሰላም ማግኘት ችለናል። አሁን ደግሞ በመንግስት እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት መካከል በሚደረጉ ንግግሮች ውስጥ ተሳታፊ ነን። የምንፈልገውን ውጤት እናመጣለን ብሎ መንጋር ከባድ ነው። አሜሪካ ያለ ሰው በአጭር ጊዜ ምላሽ ማግኘት ይፈልግ ይሆናል። ነገር ግን ድርድሩ በጣም አስቸጋሪ ነው። ዳሬሰላም የቆዩት ለሁለት ሳምንት ከግማሽ ነበር። ግን መሻሻሎች ታይተዋል" ብለዋል።

አክለውም "መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁለቱም ወገኖች አንዳንድ ፍላጎታቸውን ለመተውና ለመስማማት፣ ጦርነት መፍትሄ አለመሆኑን ለመወሰን እንዲሁም፣ ለህዝባቸው የሚበጀው እና ሰፊ አላማቸውን የሚያሳካው ወደ ፓለቲካ ውይይት መግባት መሆኑን ለመወሰን የሚያስችል ብርታት ያስፈልጋቸዋል" ሲሉ አብራርተዋል።

ሌላው በምክር ቤቱ አባላት አፅንዖት ለተሰጠው እና፣ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ያደረሱ ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡ የአሜሪካ መንግስት ምን ማድረግ ይችላል ለሚለው ጥያቄ፣ አምባሳደር ሐመር ይህ ሀላፊነት የኢትዮጵያ መንግስት እና የጦር ሰራዊታቸው የጦር ወንጀሎችን የፈፀሙት የኤርትራ መንግስት ኃላፊነት መሆኑን አስረድተው የአሜሪካ መንግስት ግን ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል። በኢትዮጵያ እንዲካሄድ ለሚታሰበው የሽግግር ፍትህ ሂደትም አሜሪካ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገች መሆኑን አመልክተዋል።

"ፍትህ እንዲሰፍን እና ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ ከመፈለግ አንፃር ትዕግስት እንደሌለን አውቃለሁ። ነገር ግን በሁሉም እርከን የሚገኙ የመንግስታችን ኃላፊዎች፣ ከኢትዮጵያ መንግስት እና የሽግግር የፍትህ ሂደቱን ለማሻሻል ኃላፊነት ካለባቸው አካላት ጋር እየተነጋገረ፣ ሁሉን ያካተተ የሽግግፍ ፍትህ እንዲኖር ግፊት ያደርጋል። በተጨማሪም ውስጥ ለውስጥ የተጀመሩ ሂደቶች አሉ። እኛም ይህ ሂደት ተዓማኒ እና ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ድጋፍ እና ምክር እንሰጣለን።"

አሜሪካ አቋርጣ ስለነበረውና በቅርቡ በቀጠለችው ለኢትዮጵያ የምትሰጠው የምግብ እርዳታ ዙሪያም ከምክርቤቱ አባላት ጥያቄ ተነስቷል። ቤክልማንም እርዳታው የቀጠለው የኢትዮጵያ መንግስ በስርጭቱ ሂደት ላይ መሰረታዊ ለውጦችን ለማድረግ ከተስማማ በኃላ መሆኑን በምሳሌ አብራርተዋል።

"የኢትዮጵያ መንግስት እህሎች የሚቀመጡበትን መጋዘኖች የማስተዳደር እና የስርጭት ሂደቱ በአጋር ተቋም ስር እንዲሆን እና የወፍጮ እና ሌሎች ተመሳሳይ ስፍራዎች ለክትትል ክፍት እንዲሆን ፈቅዷል። በተጨማሪም ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ተጋላጭነትን መሰረት ያደረገ የእርዳታ አቅርቦት እንዲኖር ተስማምቷል። ይህም ተጎጂዎችን በጋራ የመለየት እና የመጨረሻውን የተጠቃሚዎች ዝርዝር በጋራ የማፅደቅ ስራን ይጨምራል።"

በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት ያስቆመው የሰላም ስምመንት ከተፈረመ በኃላ አሜሪካ በትግራይ ክልል የተሻለ የእርዳታ አቅርቦት እና ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ከፍተኛ ድጋፍ ማድረግ መቻሉን ያመለከቱት ቤክልማን፣ አሜሪካ በምትደግፋቸው ፕሮግራሞች በኩል፣ በተለይ በክልሉ ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ወደ 100 ሺህ የሚጠጉ ሴቶች የምክር አገልግሎቶችን ጭመሮ ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል ግን በአሁኑ ሰዓት ሰብዓዊ ድጋፎችን ማድረግ አዳጋች መሆኑን ጠቅሰዋል።

"በተወሰኑ የአማራ እና ኦሮሚያ አካባቢዎች ሰብዓዊ ተግባራትን ማከናወን አስቸጋሪ እና እጅግ በጣም አደገኛ ነው። መሬት ላይ ያሉ ሰዎች ተከታታይ ማስፈራሪያዎች ይደርሷቸዋል። ስለዚህ በእነዚህ አካባቢዎች አገልግሎቶችን የመስጠት ሂደትን በተመለከተ የዕለት ተዕለት ሁኔታዎችን እያስዩ ነው የሚወስኑት። እኛም አካባቢዎቹ ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ግፊት ማድረጋችንን እንቀጥላለን።"

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ሐመር እና የዩኤስ አይዲው ቤክልማን ለምክርቤቱ በሰጡበት ወቅት በምክርቤቱ ተገኝተው የተከታተሉት የቀድሞ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለስልጣን ብርሃነመስቀል ነጋ ከአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ካሮል ቫን ዳም ጋር ባድረጉት ቆይታ አጠቅላይ የምስክርነቱ ሂደት ከአመት በፊት በቆመው ጦርነት ላይ ማተኮሩን ተችተዋል።

"ትግራይ ውስጥም ግጭት በነበረበት ወቅት እኮ ጦርነቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተዛምቷል። አሁን ደግሞ ከ40 ሚሊየን ህዝብ በላይ በሚኖርበት የአማራ ክልል ውስጥ ሰፊ ግጭት አለ። በሌሎች በኦሮሚያ እና ጋምቤላ ክልሎችም ግጭት አለ። ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት፣ በአፍሪካ ሁለተኛ ትልቁ ህዝብ የሚገኝባት ትልቅ ሀገር ናት።"

በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው አስከፊ ጦርነት፣ የዓለም ህዝብ አብዛኛው ትኩረት ትግራይ ክልል ላይ ብቻ በሆነበት ወቅትም የአማራ እና አፋር ክልሎች ሰፊ ጦርነት እንደተካሄደባቸው ያመለከቱት ብርሃነመስቀል፣ በተለይ በአሁኑ ሰዓት በአማራ ክልል በፋኖ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የሚካሄደው ጦርነት እያስከተለ ያለው እልቂት እና ውድመትም እኩል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

"የትግራይ ጦርነት እየተባለ የሚጠራው የሁለት አመት ጦርነት እኮ ትግራይ ውስጥ ብቻ የተካሄደ አይደለም። ከሁለቱ አመታት ውስጥ አብዛኛው ጦርነት የተካሄደው በአፋር እና በአማራ ክልሎች ውስጥ ነው። ምክንያቱም የትግራይ ኃይሎች ወደ አዲስ አበባ ለመድረስ እየገፉ ነበር። ስለዚህ በነዚህ አካባቢዎችም ከፍተኛ ውድመት ደርሷል። አሁን ደግሞ የአብይ መንግስት ሙሉ ትኩረቱን በአማራ ክልል ላይ አድርጎ ጦርነት አውጇል። አሁን እየተነጋገርን በክልሉ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል። የኢንተርኔት እና ሌላ መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎትም የለም።"

የአሜሪካ ምክርቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ፣ የአፍሪካ ንዑስ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ላይ ከአንድ ሰዓት በላይ ለሆነ ጊዜ ባካሄደው የምስክሮችን ቃል የመስማት ሂደት፣ ኢትዮጵያ ብራዚል፣ ሩስያ፣ ሕንድ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪቃ አባል የሆኑበትን ብሪክስ መቀላቀሏ ላይም ጥያቄዎች ተነስተዋል። በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች አሁንም ከኢትዮጵያ ባለመውጣታቸው ማዕቀብ መጣል ያስፈልግ እንደሆነም ተጠይቋል። እንደ ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ያሉ ሀገራት ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጡትን የሰው ሰራሽ አውሮፕላን (ድሮኖች) በተመለከተም አሜሪካ ከሀገራቱ ጋር ዲምፕሎማሲያዊ ማደረጓን እና ስጋቷን መግለጿም ተጠቁሟል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG