ሰሞኑን ጋምቤላ ውስጥ እየታየ ያለው ችግር ለብዙ ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑ ተነግሯል።
አንዳንድ የአባባቢው ነዋሪዎች በሰጡት ቃል ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ከሃምሣ በላይ ሕይወት መጥፋቱን ይናገራሉ።
ሁኔታውን አንዳንዶች የሃገሩ መሠረታዊ ነዋሪ ብሔረሰቦች የኝዌርና የአኝዋክ ግጭት ነው ይሉታል።
ሌሎች ደግሞ የደቡብ ሱዳንም ዳፋ ወይም ጦስ ለኢትዮጵያም እየተረጨ ነው የሚሉ አሉ።
አንዳንዶች የሁለቱ ብሄረሰቦች ግጭት የኖረ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ የብሄረሰቦች ግጭት ሳይሆን “የፖለቲካ ሰበብ ያለው ብጥብጥ ነው” የሚሉ አሉ።
የነፃነትና የዴሞክራሲ የሕዝቦች ጥምረት የሚባል ድርጅት ሁኔታውን “የዘር ማፅዳት” ሲል እያወገዘ ነው።
ለማንኛውም ስለሰሞኑ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተውን የነበሩ የጋምቤላ የፀጥታ ኃላፊ ግጭቱ “የሁለት ግለሰቦች ግጭት ነው” ብለውታል።
መዘዙ ግን የሁለት ሰው ግጭት ሆኖ አልቀረም። ዛሬ እዚህም እዚያም እያለ ጋምቤላን እያስጨነቃት ነው፤ ብዙ ሕይወት በልቷል።
ጋምቤላ አብዛኛቸው ደቡብ ሱዳናዊያን የሆኑ ከ280 ሺህ በላይ ስደተኞች የተጠለሉበት ክልል ነው፡፡ ሳዑዲ ስታርን ጨምሮ ብዙ ነዋይ አፍሳሾችም ዐይኖቻቸውን የጣሉበት ክልል ነው።
እስከአሁን በስደተኞች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩ ተገልጿል።
በሌላ በኩል ደግሞ መስከረም ውስጥ ተፈፅሞ ነበር ከተባለ ግድያ ወዲህ እየተካሄዱ ባሉ የበቀል ግጭቶች ብዙ ሕይወት እየጠፋ መሆኑን፣ የተገደለውንም ቁጥር እንደማያውቁ፣ የብዙ ሰው ሕይወት ሊጠፋ እንደሚችል የኢታንግ ወረዳ አስተዳዳሪ ኦኬሎ ኦባንግ በስልክ የገለፁለት ብሉምበርግ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳም ለብሉምበርግ በሰጡት ቃል በአኝዋክና በኝዌሮች መካከል በተካሄደ “የጎሣ” ባሉት ግጭት 14 ሰው መገደሉን ተናግረዋል።
ሁኔታው አሁን በቁጥጥር ሥር መዋሉን አቶ ጌታቸው አክለው ገልፀዋል።
በርካታ ቁጥር ያላቸው የደቡብ ሱዳን ተዋጊዎች እንደታጠቁ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት እየገቡ ነው የሚሉ ክሦችና ጥቆማዎች እየተሰሙ ነው። ዘገባውን ለማዳመጥ የድምጽ ፋይሉን ይጫኑ።