በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“በሐምሌ ወር ብቻ 96 ሰዎች ተገድለዋል”- ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል


የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር በዛሬው ዕለት በቁጥጥ ስር ሲውሉ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ቴሊቭዥን ላይ ስክሪን ኮፒ ተደርጎ የተወሰደ።
የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር በዛሬው ዕለት በቁጥጥ ስር ሲውሉ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ቴሊቭዥን ላይ ስክሪን ኮፒ ተደርጎ የተወሰደ።

የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመርና ሌሎች ስድስት የክልሉ ምክር ቤት አባላት በዛሬው ዕለት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ለአሜሪካ ድምፅ ገለጹ። ኮሚሽነሩ ሐምሌ 27/2010 ዓ.ም በቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት አመራር ሰጪነት በተቀነባበረ ወንጀል የ96 ሰው ሕይወት ማለፉን ተናግረዋል።

“በሐምሌ ወር ብቻ 96 ሰዎች በጂጂጋ ከተማ ተገድለዋል”- ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:14 0:00

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልልን ሲያስተዳድሩ የነበሩትና በቅርቡ ከሥልጣናቸው የተነሱት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) በመባል የሚታወቁት የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ከፍተኛ አቤቱታ የሚቀርብባቸው ሰው ነበሩ። የክልሉ ተወላጆች፣ ነዋሪዎች፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ሌሎች በሶማሌ ክልል በአቶ አብዲ መሐመድ ይፈፀማሉ ያሏቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፋ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ለአሜሪካ ድምፅ ስለሁኔታው ሲናገሩ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ የሶማሌ ክልል አመራሮች የለውጡ አካል እንዲሆኑና ችግሮቹ እንዲስተካከሉ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም ሳይሳካ እንደቀረ ጠቁመዋል።

ሐምሌ 27/2010 ዓ.ም ደግሞ በቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመርና ሌሎች አመራሮች የተቀነባበረ ወንጀል መፈፀማቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል፤ “በዚህም 96 ሰዎች ተገድለዋል፣ በጣም ብዙ ንብረት ወድሟል፣ ባንክና የግለሰቦች ንብረትተዘርፏል፣ ቤተክርሲያናት ተቃጥለዋል” ብለዋል።

በዛሬው ዕለት በቁጥጥር ስር የዋሉት አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ)ና ሌሎች ስድስት አመራሮች ለእስር የተዳረጉትም ሐምሌ 27 ቀን በክልሉ በተፈፀመው ወንጀል ምክኒያት ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ቅዳሜ ዕለት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ስለ ሶማሌ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ተጠይቀው ፤ “በክልሉ ሲፈፀም የነበረው በልቦለድ ወይም በፊልም ላይ የሚታይ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ መሆኑ ያጠራጥራል። ብዙ የሚያስደነግጡ ነገሮች እዛ አካባቢ ተከናውነዋል። ለምሳሌ በማረሚያ ቤት ከሚታረሙ ሰዎች ጋር አንበሳ፣ጅብና ነብር ይታሰራል። ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ብሎ ማሰብ ይከብዳል” ብለዋል።

አያይዘውም፤ “ስዎች ይታሰራሉ፣ ይዘረፋሉ፣ ይገደላሉም” ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ጉዳይ በይፋ ከመናገራቸው ቀድም ብሎ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ወች “ልክ እንደ ሞቱት ነን” በሚል ርዕስ ባለ 88 ገጽ ሪፖርት አውጥቶ ነበር። በሶማሌ ክልል “ኦጋዴን” በሚል በሚታወቀው እስር ቤት ውስጥ ዜጎች በዘፈቀደ ለዓመታት ታስረው አሰቃቂ ስቃይ እና ድብደባ እንደሚፈፀምባቸው ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱ አያይዞ፤ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግሥት በኦጋዴን እስር ቤት የሚፈጸም ማሰቃየት እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዘግናኝ እና ያልተቋረጠ ሰቆቃ፣ ድብደባ፣ ማዋረድ፣ በቂ ያልሆነ የሕክምና አገልግሎት፣ በቂ ያልሆነ የቤተሰብ እና የጠበቃ ጉብኝት ይባስ ብሎም አንዳንዴ በቂ ምግብ አለማግኘት በእስር ቤት መፈጸሙን ያትታል። ይህንን ሰቆቃም በመብት ጥሰት የታወቁት የሶማሌ ልዩ ፖሊስ እና የማረሚያ ቤቱ የጸጥታ ሀይሎች ፈፅመውታል ብሏል በሪፖርቱ።

ድርጅቱ ይህንን ሪፖርት ለማዘጋጀት የተለያዩ መረጃዎችን በግብዓት መጠቀሙን ጠቅሶ ፤የመንግስት የጸጥታ ኃይሎችን፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባላሥልጣናትንና 70 የቀድሞ እስረኞችን ጨመሮ በአጠቃላይ ለ100 ሰዎች ቃለ መጠይቅ ማድረጉን አስታውቋል።

ድርጅቱ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸውና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው የተቀየረ የቀድሞ እስረኞች ጠቅሶ በሪፖርቱ ላይ እንዳሰፈረው፤ እስረኞቹን በመላው እስረኞች ፊት ልብሳቸዉን አስወልቀው እርቃናቸውን አድረገው እንደ ደበደቧቸው ያስረዳል።

የሂዩማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፌሊክስ ሆርን ድርጅታቸው ያወጣውን ሪፖርት አስመልክቶ ከአሜሪካ ድምፅ ተጠቀው፤ የሶማሌ ክልል እስረኞችን ፍርድቤት ባለማቅረብ በሀገሪቱ ካሉት ከሌሎች እስር ቤቶች የተለየ ነው ብለዋል።

የሶማሌ ክልል ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር አቶ ኢድሪስ እስማኤል ከቪኦኤ የሶማሌኛ ቋንቋ ዝግጅት ክፍል ተጠይቀው። “ድርጊቱ በክልሉ አልተፈፀመም” ሲሉ አስተባብለው ነበር።

የፌደራል ቃቤ ሕግ የቀድሞውን የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመርን በቁጥጥር ስር ያዋለበትን የወንጀል ድርጊት ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሲዘረዝር ፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ በብሔር ግጭት ቀስቃሽነት፣ በኃይማኖት መካከል ግጭት እንዲፈጠር አድርገዋል የሚል ነው።

ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል በቁጥጥር ስር የዋሉት እስረኞች ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ አረጋግጠዋል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG