ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አሕመድ የጀመሩትን ለውጥ ለማበረታትና ለመደገፍ በተጠራውና ወደ 4 ሚሊዮን የሚገመት ተሳታፊ ተገኝቶበታል በተባለው በዛሬው ሰልፍ ላይ በተወረወረ የእጅ ቦንብ 98 ሰዎች መቁሰላቸውን የፌደራልና አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። ከእነዚህ ውስጥ ዐሥራ አምስቱ ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ መካከለኛና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማልን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ካደረጉበት መድረክ ትንሽ ራቅ ካለ ቦታ ላይ ለጊዜው ዐይነቱ ያልታወቀ ቦንብ በመፈንዳቱ አደጋው መድረሱን ተናግረዋል።
ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምሕሩ ስዩም ተሾመ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፤ የእጅ ቦንቡ በስተቀኝ በኩል ከነበሩ ታዳሚዎች አካባቢ ወደ መድረኩ ለመወርወር የተደረገው ሙከራ በአንድ ሌላ ታዳሚ የወርዋሪው እጅ በመያዙ እዛው ሊፈነዳ እንደቻለ ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን ጨርሰው ለስንበት ተንቀሳቅሰውበት በነበረው አቅጣጫ ሊወረወር እንደነበር የገለፁት አቶ ስዩም ተሾመ፤ "እንደታሰበው ባለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ምንም ዓይነት አደጋ ሳይደርስ ቀረ" ብለዋል።
"መድረኩ ላይ ስለነበርኩ ወደታች ይታየኝ ነበር። ከመፈንዳቱ በፊት ትንሽ ግርግር ነገር አይቻለሁ።" ብለዋል።
ፍንዳታውን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ግርማ ካሳ፤ ፍንዳታው በዐሥራ አምስት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ሲያደርስ በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ መካከለኛና ቀላል ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
ከፍንዳታው በተጨማሪ በመገፋፋት፣ በመረጋገጥ በመውደቅ ጭምር አደጋ መድረሱንም ተናግረዋል። ኮሚሽነሩ በሰልፉ ተሳታፊዎች ቁጥር ከተማዋ ከዚህ ቀደም ካስተናገደቻቸው ሰልፎች በእጅጉ የላቀ ነው ብለውታል።
ከቆሰሉት ሰዎች መካከል በጥቁር አንበሳና በዘውዲቱ ሆስፒታል የሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑንን ከሆስፒታል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ በአሁኑ ሰዓት አምስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመውናል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ