በዚህ የአውሮፓውያኑ ዓመት ብቻ፣ አያሌ የአውሮፓ አገሮችን እስኪያጨናንቅ ድረስ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች ናቸው ሜዲትሬንያን ያቋረጡ። ባለፈው ሚያዝያ ወር ለምሳሌ፣ አውሮፓ ለመግባት ያቀዱ 80 ፍልሰተኞች ሊብያ ውስጥ ባሕር ሰጥመው አስከሬናቸው በማልታ በኩል መገኘቱ ይታወሳል።
ያ አሰቃቂ ሁኔታ ነው ለአሁኑ የማልታ ጉባዔ መካሄድ ሚክናት የሆነው። እናም የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች፣ አፍሪቃ ውስጥ ያለውን ፍልሰተኛነት ከምንጩ ለማድረቅ ይቻል ዘንድ የ$1.9 ቢልዮን ርዳታ አጽድቀዋል።
ገንዘቡ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የጤና ጥበቃ ይዞታውን ለማሻሻልና ግጭቶችን ለማስቀረት ይውላል ነው የተባለው። በዚሁ ወቅት የአውሮፓ መሪዎች ቀውሱን ለመቋቋም ይረዳል ያሉትን ባለ ፲፯ ገጽ «የድርጊት ፕሮግራም ወይም ዕቅድ» ይፋ አድርገዋል። ይህ ፕላን ግን የተለያዩ አስተያየቶችን አስነስቷል። የኒዠሩ ፕሬዚደንት ማሃማዱ ኢሶፉ (Mahamadou Issoufou)"በቂ አይደለም። 1.8 ቢልዮን ዩሮው እንኳን በቂ ልሆን ተቀራራቢም አይሆንም። ችግሩ በጣም ሰፊ ነው። ለዚህም ነው፣ በዕርዳታ አሰጣጡ እረገድ ሌሎች ተባባሪዎችን የምንጠይቀው" ብለዋል።
የኒዠሩ ፕሬዚደንት ማሃማዱ ኢሶፉ (Mahamadou Issoufou)
የኢጣልያው ጠቅላይ ሚኒስትር ማተዮ ረንዚ (Matteo Renzi) በበኩላቸው"እነዚህ አስተያየቶች ሁሌም የሚመጡት፣ አሉታዊ አመለካከት ካላቸው ወገኖች ነው። እኔ ግን ዛሬ እያየሁ ያለሁት፣ አዎንታዊ ሁኔታዎችን ነው። ሚክናቱም፣ በአንደኛ ደረጃ የስደተኛነትን ቀውስ በመቋቋም እረገድ ኢጣልያ ብቻዋን አይደለችም። በሁለተኛ ደረጃ አፍሪቃ ቀዳሚዋ አህጉር ነች" ሲሉ ተደምጠዋል።
አኃዙ የሚያሳየው ግን፣ አፍሪቃ ቀዳሚ መሆኗን አይደለም። የውጪ ልማት ተቋም ተወካይ ማርታ ፎረቲ (Marta Forest)"ሦስት ቢሊዮኑ ዩሮ ለቱርክ እንዲሰጥ ቃል ተገብቶ ነበር። ያም ሦርያውስጥ ያለውን የወቅቱን ቀውስ ለማቆም የምታደርገውን እርዳታ ለማገዝ ነው። በዚያ ስሌት ስናየው፣ ለመላው አፍሪቃ አህጉር እ1.8 ቢልዮን ዩሮ ወይም ደግሞ $1.9 ቢልዮን በቂ ሊሆን አይችልም" በማለት አክለዋል።
አውሮፓ በተጨማሪም፣ ለአፍሪቃ ልማት በምትሰጠው እርዳታ ፈንታ፣ ከእያንዳንዳቸው የአፍሪቃ አገሮች ጋር የፍልሰተኞች ስምምነት ለመፈራረምም ታስባለች።
የሜዲትሬንያንን ባሕር የሚያቋርጡ ፍልሰተኞች ቁጥር ግን፣ በጣም ቀንሷል። ይህም፣ በቱርክ እና በግሪክ በኩል አብዛኛዎቹ ሦርያውያን የሆኑበት 650,000 ሰዎች ገብተዋል።
ለስደተኞች መብት በመቆም ለረዥም ጊዜ የምትታወቀው ስዊድን፣ በዚህ ሳምንት አዲስ ጊዜያዊ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ አስተዋውቃለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስተፋን ሎፍቨን (Stefan Lofven) "አውሮፓ ውስጥ ያሉትን ህጎች ነው የምንከተለው። ባለሥልጣኖቻችን ለደኅንነት ዋስትና መስጠት እንደማንችልና ድንበሮቻችንን እንድንቆጣጠር ሲነግሩን መስማትና ያን ማክበር ይኖርብናል" ብለዋል።
የስዊድን አቋም፣ አውሮፓ ውስጥ ያለ ፓስፖርት ለመንቀሳቀስ ያለውን መጻዒ ሁኔታ ጥርጣሬ ውስጥ እንደከተተው ታዛቢዎች ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ኤክኖሚ ከመላው አፍሪቃ የበለጸገ ሆኖ፣ በያመቱ ግን፣ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፣ በሺህዎች የሚቀሩ፣ ወደ አውሮፓ፣ ሰዑዲ አረቢያና ወደ ደቡብ አፍሪቃ ይፈልሳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ የብዙ ፍልሰተኞች መዳረሻ አገርም ነች።
የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ የተረጋጋ ባለመሆኑ፣ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያን ማረፊያ የሚያደርጉ ፍልሰተኞች የሚመጡት ከሱዳን፣ ከኤሪትራና ከሶማልያ ነው።
"ይህ አሁን የሚታየው የስደተኞች ሁኔታ ኢትዮጵያ ላይ ያለው አንደምታ ቀላል አይደለም» ይላሉ የኢጋዱ ሪቻርድ ባርኖ (Richard Barno) እንደ ሱዳንና ኤሪትራ ባሉ ጎረቤት አገሮች የሚታየው የሴኩሪቴ ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ መረጋጋት ላይ፣ ቀላል ያልሆነ ተጽዕኖ ነው ያለው።
30% የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን፣ የቀን ገቢያቸው ከ$1 ያነሰ ነው። እናም ከአገር የመፍለሳቸው ሚክናት ከኑሮ ውድነት ጋር ይያያዛል። ኦስትሪያ ውስጥ እአአ በ2013 ዓም ፪፻ ኢትዮጵያውያን ጥገኝነት ጠይቀዋል። ኤሪትራውያን ደግሞ ፶፱ ነበሩ።
ከአውሮፓና ከመካከለኛው ምሥራቅ በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች የተዘወተረው አካሄድ ግን ወደ ደቡብ አፍሪቃ ነው። በየትም ይሁን በየት ግን የኢትዮጵያ መንግሥት የትኛውንም ዓይነት ፍልሰት አይደግፍም። ህገ-ወጥ የሰዎች መናገድን ለማቆምም ደንብ አውጥቷል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የአውስትሬልያ የስደተኞች ፖሊሲ በተመድ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ አካል በጽኑ ተወግዟል። ይህ ትችት የተሰነዘረው፣ ባለሥልጣናት እንደገለጡት በአንድ ፍልሰተኞች በተከማቹበት ማዕከል ብጥብጥ ከተነሳ በኋላ ነው።
የአውስትሬልያው ባለሥልጣን ስቲቭ መግልን (Steve McGlynn) እንደገለጹት ግን፣ ይህ ፍልሰተኞቹን በአንድ ስፍራ ማቆየት፣ ባሕር በማቋረጥ ሕይወታቸውን ከአደጋ ለመታደግ የታቀደ ዘዴ ነው። ሙሉውን ዝርዝር ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።