በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዓለም የጎዳና ላይ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸነፉ


በዓለም የጎዳና ላይ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸነፉ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:46 0:00

በዓለም የጎዳና ላይ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ ክብረ ወሰን በማሻሻል አሸነፉ

ለመጀመሪያ ጊዜ በላቲቪያ ሪጋ በተካሔደው የዓለም የጎዳና ላይ ውድድር፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያየ ርቀት የሻምፒዮናው አሸናፊ ኾነዋል። አትሌት ድርቤ ወልተጂ፣ በአንድ ማይል የሴቶች የጎዳና ላይ ሩጫ ክብረ ወሰን በመያዝ አሸንፋለች።

አትሌት ድርቤ ወልተጂ፣ በሴቶች አንድ ማይል ርቀት፣ በ4:21:00 በኾነ ሰዓት የዓለምን ክብረ ወሰን በማሻሻል በቀዳሚነት ስታሸነፍ፣ ፍሬ ወይኒ ኀይሉ 4:23:06 በመግባት ሁለተኛ ኾና ጨርሳለች።

በርቀቱ ለመጀመርያ ጊዜ ተሳትፋ ያሸነፈችው አትሌት ድርቤ፣ የዓለምን ክብረ ወሰን በማሻሻልዋ በእጅጉ እንደተደሰተች ተናግራለች።

በውድድሩ ድርቤን ተከትላ የገባችው አትሌት ፍሬ ወይኒ ኃይሉ በበኩሏ፣ ከድርቤ ጋራ ተከታትለው በመግባት አሸናፊ በመኾናቸው፣ "ደስ ብሎኛል፤" ብላለች።

በሌላ በኩል፣ በወንዶች የአምስት ኪሎ ሜትር የዓለም የጎዳና ውድድር፣ አትሌት ሐጎስ ገብረ ሕይወት የወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ፤ አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ የብር ሜዳልያ አሸንፏል፡፡

አትሌት ሐጎስ ገብረ ሕይወት ርቀቱን ለመጨረስ 12ደቂቃ ከ59 ሰከንድ ሲፈጅበት፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ ደግሞ በ13 ደቂቃ ከ2 ሰከንድ ርቀቱን አጠናቋል፡፡

ከውድድሩ በኋላ አትሌት ሐጎስ ገብረ ሕይወት እና ዮሚፍ ቀጄልቻ በሰጡት አስተያየት፣ የአየሩ ኹኔታ ነፋሳማ እንደነበረ ጠቅሰው፣ በመጣው ውጤት ደስተኛ እንደኾነ ተናግረዋል።

የአትሌት ሐጎስ ገብረ ሕይወት ኣሠልጣኝ ኮማንደር ቶሌራ ዲንቃ በሰጡን አስተያየት፣ ለውድድሩ በተመደበው ጊዜ ከኢትዮጵያ ተነሥተው ፍራንክፍርት ላይ ቢደርሱም፣ ለቡዙ ሰዓት እንደተጉላሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ይህም ኾኖ በመጣው ነጥብ ደስተኛ እንደኾኑ ተናግረዋል።

በሴቶች የአምስት ኪሎ ሜትር የዓለም የጎዳና ላይ ውድድር፣ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች፡፡ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ርቀቱን ለመጨረስ፣ 14 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ ፈጅቶባታል፡፡

ሌላዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መዲና ኢሳ፣ አምስት ኪሎ ሜትሩን በ14 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ በማጠናቀቅ አራተኛ ወጥታለች። መዲና፣ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሰዓት ሲቀረው የመውደቅ ኣደጋ ባያጋጥማት ሜዳልያ ውስጥ የመግባት ዕድል እንደነበራት ተናግራለች::

ከኢትዮጵያው ቡድን መሪ ኣንዱ አሠልጣኝ ጌታመሳይ፣ በተመዘገበው አጠቃላይ ውጤት ደስተኛ እንደኾኑ ገልጸው፣ "ከውድድሩም ቡዙ ተምረናል፤" ብለዋል፡፡

ትላንት እሑድ፣ በላቲቪያ ሪጋ በተካሔደው በዚኹ የዓለም የጎዳና ውድድር ላይ ውድድር፣ ከ100 በላይ የዓለም ሀገራት ተሳትፈውበታል።

ለኢትዮጵያ፣ በሴቶች እና በወንዶች አንድ ማይል ርቀት ውድድር፣ ክብረ ወሰን መሻሻሉ ከቀደሙት የተለየ ያደርገዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG