በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

 
ለ“ኦሮሚያ ጸጥታ” በሚል በተቋቋመ ኅቡእ ኮሚቴ የዘፈቀደ ግድያና እስራት ተፈጽሟል- ሮይተርስ

ለ“ኦሮሚያ ጸጥታ” በሚል በተቋቋመ ኅቡእ ኮሚቴ የዘፈቀደ ግድያና እስራት ተፈጽሟል- ሮይተርስ


ለ“ኦሮሚያ ጸጥታ” በሚል በተቋቋመ ኅቡእ ኮሚቴ የዘፈቀደ ግድያና እስራት ተፈጽሟል- ሮይተርስ
please wait
  • Auto
  • 240p
  • 360p
  • 480p
  • 720p

No media source currently available

0:00 6:26 0:00
  • Auto
  • 240p
  • 360p
  • 480p
  • 720p

ለ“ኦሮሚያ ጸጥታ” በሚል በተቋቋመ ኅቡእ ኮሚቴ የዘፈቀደ ግድያና እስራት ተፈጽሟል- ሮይተርስ

በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውን ታጣቂ ቡድን ለመደምሰስ በሚል፣ በክልላዊ መንግሥቱ የተቋቋመና የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚገኙበት ምስጢራዊ ኮሚቴ፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ሕገ ወጥ እስር እንዲፈጸም ማዘዙን “ባካሔድኹት ምርምራ ደርሼበታለሁ” ሲል ሮይተርስ ዘገበ።

ሮይተርስ፣ ዛሬ ዐርብ ባወጣው ልዩ ዘገባው፣ ከሠላሳ የሚበልጡ በፌዴራል እና በክልል ባለሥልጣናት፣ ዳኞች እና ጠበቆች የተፈጸሙ ጥቃቶች ሰለባዎችን ማነጋገሩን አመልክቷል። በተጨማሪም፣ በክልሉ የፖለቲካ እና የፍትሕ ዘርፍ ኃላፊዎች የተረቀቁ ሰነዶችንም መመርመሩን ገልጿል።

ምስጢራዊ ኮሚቴው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ2010 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን ከመጡ ከወራት በኋላ ሥራ እንደጀመረና ስሙም በአፋን ኦሮሞ “ኮሬ ነጌኛ” እንደሚባል ገልጿል፡፡ በቋንቋው የስሙ ቀጥተኛ ትርጉም “የሰላም ኮሚቴ” ማለት ቢኾንም፣ የሮይተርስ የምርመራ ዘገባ ግን “የጸጥታ ኮሚቴ” እያለ ነው የጠቀሰው፡፡

ኅቡእ ኮሚቴው ምን እያደረገ እንደሆነ፣ ያካሔዳቸው ቃለ መጠይቆች እና የመረመራቸው ሰነዶች ለመጀመሪያ ጊዜ ግልጽ አድርገው ማሳየታቸውን፣ ሮይተርስ በልዩ የምርመራ ሪፖርቱ ላይ አስፍሯል። የጸጥታ ኮሚቴው መኖር ከዚህ ቀደም ተዘግቦ እንደማያውቅም አክሎ አመልክቷል።

የኮሚቴው ተግባር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያደርጓቸዋል የተባሉ ጥረቶች ዋና አካል እንደኾነ፣ የሮይተርስ ልዩ ዘገባ አመልክቷል። እኒህም፣ የኦሮሞ ሕዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እንዲሁም ቋንቋው እና ባህላዊ መብቱ በይበልጥ እንዲከበሩለት፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ለዓመታት ሲያካሒድ የቆየውን የትጥቅ ዐመፅ ማስቆም እንደኾኑ፣ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸውና አሁንም በሥራ ላይ ያሉና የቀድሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት መናገራቸውን ጠቅሷል፡፡

ኦሮሞዎች “በፖለቲካ እና በማኅበራዊ ኑሮ ተገልለናል፤” በማለት ለረጅም ጊዜ ቅሬታ ሲያሰሙ መኖራቸውን ሪፖርቱ አውስቷል፡፡ በ2011 ዓ.ም. እንደ አዲስ ተቃውሞ በተቀሰቀሰ ጊዜ መንግሥት ተቃውሞውን ለማስቆም የወሰደውን ከባድ ርምጃ የመራው “ኮሬ ነጌኛ” እንደሆነ፣ አምስቱ ባለሥልጣናት እንደገለጹለት ሮይተርስ አመልክቷል።

ልዩ ዘገባው አስከትሎም፣ በኦሮሚያ ክልል ባለው ሁከት ምክንያት ብዙ መቶ ሺሕ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውን ገልጾ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትና የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች፣ ከ2011 ጀምሮ በሚደርሱት ግድያዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ጠቁሟል። ቡድኑ ውንጀላውን ያስተባብላል።

ሮይተርስ እንዳስታወቀው፣ ከልዩ ዘገባው ምንጮች አምስት የቀድሞ እና የአሁን ባለሥልጣናት መካከል አንዱ ማንነታቸው እንዲገለጽ የፈቀዱ ሲሆን፣ ቀድሞ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት ሚልኬሳ ገመቹ ናቸው።

በ“ጸጥታ ኮሚቴው”(ኮሬ ነጌኛ) ስብሰባዎች የተካፈሉ ሁለት ሰዎችን ጨምሮ የተቀሩት ግን ማንነታቸው እንዳይገለጽ ጠይቀዋል።

ስለኅቡእ ኮሚቴው እንቅስቃሴዎች የሚያውቁት እነዚህ ሰዎች፣ በክልሉ የደረሱት ብዛት ያላቸው ግድያዎች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እስር፣ በኮሚቴው ትዕዛዝ የተፈጸሙ እንደሆኑ ነግረውኛል፤ ብሏል። በ2013 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በ14 እረኞች ላይ የተፈጸመውንና መንግሥት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎችን የወነጀለበትን ግድያ መጥቀሳቸውንም አመልክቷል።

ሮይተርስ ክትትሉን ተመርኩዞ ያጠናቀረውን ሪፖርት፣ ለኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ ማቅረቡን ገልጾ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ “ኮሬ ነጌኛ” የተባለው የጸጥታ ኮሜቴ መኖሩን አረጋግጠውልኛል፤ ብሏል። ኅቡእ ኮሚቴው የተቋቋመበት ዓላማ፣ በኦሮሚያ ክልል እየተባባሰ ለቀጠለው የጸጥታ ችግር መፍትሔ ለመፈለግ ቢኾንም፣ ከተመሠረተበት ዓላማ ውጭ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን በስፋት በመፈጸም በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ጣልቃ እየገባ ነው፤ ማለታቸውን ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽሕፈት ቤት እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት፣ ይህን ዘገባ አስመልክቶ በዝርዝር ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ አለመስጠታቸውን ሮይተርስ አስታውቋል።

በማስከተልም፣ ስለ መንግሥታቸው የሰብአዊ መብቶች አያያዝ የሚከራከሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ በቅርቡ ለሀገሪቱ የፓርላማ አባላት ጥያቄ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ “በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የምንመራ በመኾናችን ሰውን መረሸን ይቅርና ልናስር እንኳን አንችልም፤” ማለታቸውን ጠቅሷል፡፡

የሮይተርስ ዘገባ በይቀጥላልም፣ የኦሮሚያው ዐመፅ በአገሪቱ የቀጠለውን አለመረጋጋት የሚያስታውስ እንደሆነ አመልክቶ፣ በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት በብዙ መቶ ሺሕዎች ሰዎች የተገደሉበት ጦርነት ከተካሔደ በኋላ የሰላም ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውሷል፡፡ በአማራ ክልል፣ ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ በመንግሥቱ የጦር ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ውጊያ እየተካሔደ መሆኑንና የፌዴራሉ መንግሥት በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማውጣቱን ገልጿል።

የፌዴራሉ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ እ.አ.አ ባለፈው 2023 መባቻ የሰላም ንግግር ከጀመሩ ወዲህም ሳይቀር በክልሉ ሁከቱ መቀጠሉን ሪፖርቱ ጠቁሟል። ታጣቂ ቡድኑ በኢትዮጵያ መንግሥት በአሸባሪነት እንደተፈረጀ ሪፖርቱ አስታውሶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግን በተፈረጀበት የአሸባሪነት ሥያሜ እንደማይጠሩት አስፍሯል።

ኮሬ ነጌኛ ስብሰባውን የሚያካሒደው በኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሲኾን፣ በሊቀ መንበርነት የሚመሩትም የወቅቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት እና የቀድሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጽሕፈት ቤት ሹም የነበሩት ሽመልስ አብዲሳ መሆናቸውን፣ ያነጋገራቸው የቀድሞ እና የአሁን ባለሥልጣናት እንደገለጹለት ሮይተርስ አመልክቷል፡፡

የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ አመራር አባል ፈቃዱ ተሰማ፣ የክልሉ ዋና የጸጥታ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ እና ሌሎችም የክልሉ የፖለቲካ እና የጸጥታ ባለሥልጣናት፣ የኮሚቴው አባላት እንደኾኑ ምንጮቹ እንደገለጹለት ሮይተርስ አመልክቷል፤ አንዳቸውም ግን ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጡም፤ ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በኮሚቴው ስብሰባዎች ላይ ተገኝተው ወይም ለኮሚቴው ትዕዛዝ ሰጥተው ያውቁ እንደኾን አንዳችም ማስረጃ አለማግኘቱን ሮይተርስ አስታውቋል፡፡ አክሎም፣ ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ ሰዎች፣ የጸጥታ ኮሚቴው የተቋቋመው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳሳቢነት እንደሆነ ነግረውኛል፤ ብሏል፡፡

በ2014 ዓ.ም. ማለትም በጎርጎርሳውያኑ በ2022 መጀመሪያ ላይ፣ ስለ ኮሚቴው እንቅስቃሴ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያንስ አንዴ ገለጻ እንደተደረገላቸው፣ በወቅቱ በቦታው የነበሩ ሰው እንደገለጹለት ያመለከተው የሮይተርስ የምርመራ ዘገባ፣ በነጻ ምንጮች ግን ለማረጋገጥ እንዳልቻለ አስታውቋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG