በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ታዋቂዎቹ እስረኞች የይቅርታ ፎርም እንደማይፈርሙ መግለፃቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ


ዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዱዓለም አራጌንና አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)
ዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዱዓለም አራጌንና አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አንዱዓለም አራጌንና አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ) ከእስር ለመፈታት የግንቦት ሰባት አባል መሆናቸውን አምነው የይቅርታ ፎርም ላይ እንዲፈርሙ መጠየቃቸውን ለቤተሰቦቻቸው ገለፁ። በሌላ በኩል በይቅርታ እንዲፈቱ የተወሰነላቸው 417 ታራሚዎች ዝርዝር ለውሳኔ ወደ ሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር መላኩን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ምንጮች ገልፀዋል፡፡

ታዋቂዎቹ እስረኞች የይቅርታ ፎርም እንደማይፈርሙ መግለፃቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:00 0:00

ቤተሰቦቻቸው ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፤ እስረኞቹ “የግንቦት ሰባት አባል ሳንሆን እንዴት ነን ብለን እንፈርማለን፤ መንግሥት ይቅርታ ሊጠይቀን ሲገባስ እንዴት ይቅርታ እንጠይቃለን?” የሚል መልስ ሰጥተው ፎርሙ ላይ ለመፈረም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

ጋዜጠኛ እስክንደር ነጋና አቶ አንዷለም አራጌን ጨምሮ 746 እስረኞች በይቅርታና ክሳቸው ተቋርጦ እንዲለቀቁ መወሰኑ በትናንትናው ዕለት የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉን ጠቅሰው ከዘገቡ በኋላ ዜናው በሁሉም መንገድ ሲሰራጭ ውሏል።

ይህን ዜና መስማታቸው እንዳስደሰታቸው የገለፁልን የእስረኞቹ ቤተሰቦች በዛሬው ዕለት ሊጠይቋቸው ሲሄዱ ከእስር ለመፈታት ቅድመ ሁኔታ እንደቀረበላቸው መናገራቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የጋዜጠኛ እስክንደር ነጋ ባለቤት ሰርካለም ፋሲል የምትገኘው እዚህ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሲሆን በዛሬ ዕለት ሊጠይቁት ከሄዱት ቤተሰቦቿ ደስታዋን የሚቀይር የትናንቱን ተቃራኒ ዜና መስማቷን ትናገራለች።

ዛሬ አቶ አንዷለም አራጌን ለማነጋገር እስር ቤት እንደሄደች የገለፀችልን እህቱ ፋንቱ አራጌም ከወንድሟ ተመሳሳይ መልስ መስማቷን ገልፃልናለች።

የአቶ አንዷለም አራጌ ባለቤት ዶ/ር ሰላም አስቻለውም በትናንትናው ዕለት ስናነጋግራት“ዜናውን አላዳመጥኩም ሰዎች ናቸው ደውለው የነገሩኝ። ስሙ ተጠርቷል ብለው ነው በደንብ አስረግጠው የነገሩኝ። እኔ ግን ከሰማሁ ወይም ካየሁ በኋላ ነው የማረጋግጠው” የሚል ምላሽ ሰጥታን ነበር ዛሬ ማምሻው ደውዬላት ነበር። እርሷ እስር ቤት ባለመሄዷ መረጃውን ከእህቱ እንዳገኘች ትገልፃለች።

ከእስክንድር ነጋና አንዷለም አራጌ ጋ አብሮ የተነገረው የመላው ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) አመራር አባል አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ ወይም (አበበ ቀስቶ) እንደሆነ ታውቋል። አቶ ክንፈ ሚካኤል በሽብር ወንጀል ተከሶ 25 ዓመት ከተፈረደበት በኋላ በይግባኝ ወደ 16 ዓመት ዝቅ የተደረገለት ፍርደኛ ነው።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና የቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አንዷለም አራጌ ብቻ ናቸው። ሁለቱም መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም መታሰራቸው የሚታወስ ሲሆን ጋዜጠኛ እስክንድር 18 ዓመት አቶ አንዷለም አራጌ ደግሞ ዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው ይታወሳል።

ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ደህንነት ተሟጋች ቡድን /ሲፒጄ/ የአፍሪካ ቀንድ ተከራካሪ አንጄላ ኲንታልን

ጠቅሶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሊፈታ ይገባል ብሏል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ትናንት በሰጠው መረጃ፤ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የይቅርታና የክስ ማቋረጥ እንደሚያደርግ በወሰነው መሰረት የተከናወነ ነው እንደሆነ አስታውቋል።

ከዚህ ውሳኔ በኋላ ታዋቂውን ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራን ጨምሮ የተወሰኑ እስረኞች መፈታታቸው የሚታወስ ሲሆን በሀገር ውስጥ የእስረኞችን ጉዳይ የሚከታተሉ ተሟጋቾችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የኅሊናና የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን በመግለፅ ሁሉም እንዲፈቱ ሲጠይቁ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG