በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ቀን


የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች
የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች

መጋቢት ሃያ ስምንት የኢትዮጵያ አርበኞች ከሌሎችም የውጭ አጋር ኃይሎች ጋር በመሆን ሃገራቸውን ከፋሽስት ጣልያን ወራሪ ጦር ነፃ አውጥተው አዲስ አበባ የገቡበት ቀን ነው፡፡

ይህ ታሪክ ከተሠራ እነሆ ዛሬ ሰባ አንድ ዓመት ደፈነ፡፡

በአምስቱ የወረራ ዓመታት ስለተሠራው ግፍና ጥፋት ዛሬ እየተሟገተ ያለ “ዓለምአቀፍ ሕብረት ለፍትሕ - የኢትዮጵያ ጉዳይ” የተባለ ድርጅት አሜሪካ ውስጥ ተቋቁሞ ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል፡፡

ድርጅቱ ባወጣው በጥናት የተደገፈ መረጃ መሠረት በአምስቱ የወረራ ዓመታት ውስጥ አንድ ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ተገድለዋል፤ ሁለት ሺህ አብያተ ክርስቲያንና ከግማሽ ሚሊየን በላይ ቤቶች ወድመዋል፤ ዘረፋ ተፈፅሟል፤ 14 ሚሊየን እንስሣት ተገድለዋል፣ በፋሽስቱ ጦር በመላ ሃገሪቱ የተረጨው የመርዝ ጋዝ ጥፋትና የአካባቢ መበከልን አስከትሏል፡፡

የፋሽስት ጣልያን መንግሥት የከፈተው ጦርነት መንስዔ በአድዋ ጣልያን የደረሰባትን ሽንፈት ለመበቀልና ዓላማውም ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ እንደነበረ የሚናገረው ዓለምአቀፉ ሕብረት አሁን እያካሄደ ባለው ዘመቻው ቫቲካን ኢትዮጵያን በይፋ ይቅርታ እንድትጠይቅ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ የተፈፀመውን አድራጎት በጦር ወንጀልነት እንዲመዘግብ እና የኢጣልያ መንግሥት ለኢትዮጵያ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል እየቀሰቀሰ ይገኛል፡፡

ጉዳዩንም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለማስገባት የኢትዮጵያዊያንና ይህንን የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚደግፉ ሁሉ ሕብረቱ በኢንተርኔት በከፈተው ዌብሣይቱ www.globalallianceforethiopia.org እየገቡ እንዲፈርሙ ጠይቋል፡፡

እስከአሁንም ከሰላሣ ሃገሮች ከ2 ሺህ 500 በላይ የሚሆን ሰው መፈረሙ ተገልጿል፡፡

ለሃያ ስምንት ዓመታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ አገልግለው አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙት የድርጅቱ አስተባባሪ አቶ ኪዳኔ ዓለማየሁ ለቪኦኤ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ያነጋገራቸው ሰሎሞን አባተ ነው፤ ቃለምልልሱን ያዳምጡት፡፡

XS
SM
MD
LG