በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል የፈፀሙ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ኢሰመኮ ጠየቀ


123 ሰዎች የተገደሉበት ዘግናኝ ወንጀሎች ተፈፅመዋል ብሏል

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተፈፀመው ድርጊት በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ዛሬ የምርመራ ውጤቱን ይፋ ሲያደርስግ በዚህ አሰቃቂ ባለው ድርጊት በአጠቃላይ የ123 ሰዎች ሕይወት ማለፉንም ገለፀ።

ኮሚሽኑ ያሰባሰውን መረጃ ጠቅሶ ዛሬ አርብ ታኅሣሥ 23/2013 ዓ.ም ባወጣው ባለ 59 ገፅ ሪፖርት፤ የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ ለሦስት ቀናት በነበሩ የፀጥታ መደፍረሶች በአጠቃላይ 123 ሰዎች መገደላቸውን እና ቢያንስ 500 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።

ከሰኔ እስከ ሐምሌ 2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ 75 ሰዎች መገደላቸውን እና ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች በአካላቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጿል።

ኮሚሽኑ “በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው” ባለው በዚህ ድርጊት፤በአብዛኛው በቡድን የተደራጁ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ በብሔርና በኃይማኖት ተለይተው የተመረጡ ሲቪሎችን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ገድለዋል ብለዋል። ጥቃቱ ከተፈፀመባቸው ውስጥ ወደ 30 የሚሆኑት ታርደው እና መንገድ ለመንገድ እየተጎተቱ የማሰቃየት ተግባራት ተፈፅሞባቸው የተገደሉ ናቸውም ብሏል።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ባጠናቀረው በዚህ ሪፖርት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ፤ “ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የተቀመጡ ሰላማዊ ሰዎች ሳይቀሩ በማጥቃቱ በተሳተፉ ግለሰቦች እና ቡድኖች በጩቤ፣ በድንጋይ፣ በእሳት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ፣ በዱላ፣ በዶማ፣ በገጀራ እና በመጥረቢያ በአጠቃላይ ፍጹም ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተገድለዋል፣ ተደብድበዋል፣ የአካል ጉዳት ደርሶባቸውል” ብሏል።

“ከ6,000 በላይ የሚደርሱ ሰዎች ተፈናቅለዋል 900 በሚደርሱ ግለሰቦች፥ በንግድ ድርጅቶችና የመንግሥት ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ ተፈፅሟል” ብሏል ሪፖርቱ። ጥቃቱ የተሰነዘረው በአማራ ብሔር ተወላጆችች እና በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ነው።

“ምንም እንኳን የፀጥታ ኃይሉ በየቦታው የገጠመውን መጠነ ሰፊ የፀጥታ መደፍረስ ችግር እና የፀጥታ አባሎቹንም የሕይወት መስዋዕትነት በሚጠይቅ ሁኔታ በመሰማራታቸው ኃላፊነታቸው እጅግ ፈታኝ የነበረ መሆኑን መገንዘብ ቢቻልም፤ በተወሰኑ ቦታዎች የኃይል አጠቃቀም ተመጣጣኝነት ከፍተኛ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው” ብሏል ኮሚሽኑ።

ይህንንም በምሳሌ ሲያስቀምጡ “በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ፣ ሰልፍ ውስጥ ያልነበሩ፥ በመንገድ ወይም በቤታቸው በር ላይ የተገደሉ፣ ለማሸማገል ጣልቃ የገቡ የአገር ሽማግሌዎችን እና የአዕምሮ ህመምተኛ ጭምር እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል።” ብሏል።

በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ የአካባቢው ባለሥልጣናት ጥቃቱ ከደረሰባቸው ሰዎች ለተደወለላቸው የድረሱልን የስልክ ጥሪ፤ “ጣልቃ እንድንገባ ከበላይ አካል የተሰጠን ትዕዛዝ የለም” በማለት እንዳልደረሱላቸው ተናግረዋል። አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ጥቃቱ በሚደርስባቸው ወቅት ፖሊስ ዝም ብሎ ይመለከታቸው እንደነበር ከጥቃቱ የተረፉት እማኞቹ ለኮሚሽኑ ተናግረዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በኢትዮጵያ የሚታየው የግፍና የጭካኔ ወንጀሎች መደጋገም፣ የችግሩን ስር መሰረት ለመፍታት የሚያስችል የተሟላ ብሔራዊ የግፍና ጭካኔ ወንጀል መከላከያ ስትራቴጂ ነድፎ በአፋጣኝ በሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ የሚያሳይ መሆኑን” ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ አካባቢዎች በተከሰተ የፀጥታ መደፍረስ የተሳተፉ ሰዎችና ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ ያደረሷቸው ጥቃቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ባሕርያትን የሚያሟሉ መሆናቸውን ሪፖርቱ በማረጋገጡ አጥፊዎቹ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በሰብዓዊነት ላይ ወንጀል የፈፀሙ ሕግ ፊት እንዲቀርቡ ኢሰመኮ ጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:51 0:00


XS
SM
MD
LG