በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሂዩማን ራይትስ ዋች ባለሙያዎች ስለኢትዮጵያ ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት መመረጥ


ኢትዮጵያ ባለፈው ሣምንት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት መመረጧን ተከትሎ ከተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው፡፡ ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን ሂዩማን ራይትስ ዋች ድምፃቸውን ቀድመው ካሰሙት ወገኖች መካከል ሆኖ ይገኛል፡፡

የቡድኑ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ፈታሽና መርማሪ ፌሊክስ ሆርን ሰሞኑን ያወጣውን ፅሁፍ የጀመረው “ኢትዮጵያ እጅግ አስፈሪ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ታሪክ ያላት ሃገር ነች፤ ይሁን እንጂ በዚህ ሣምንት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባልነት እንዳትመረጥ አላገዳትም” በሚሉ ዓረፍተ-ነገሮች ነው፡፡

ሰሞኑን ከተመረጠችበት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት በተጨማሪ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባልም የሆነችው ኢትዮጵያ መንግሥት - ይላል የፌሊክስ ሆርን ፅሁፍ - በቅርብ ወራትም በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰላማዊ ተቃዋሚዎች ግድያ ላይ ተሠማርቷል፡፡

የፌሊክስ ሆርን መልዕክት ይቀጥልና ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በማሰር በአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ መካከል እንደሆነች ይናገራል፡፡ “ኢትዮጵያ ነፃ ሲቪል ማኅበረሰብ እንዳይኖር ያደረገች ወይም ያጠፋች፤ ፀረ-ሽብር ሕጓን ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈን ጉዳይ ያለአግባብ የተጠቀመች ሃገር ነች” ይላል፡፡

“ኢትዮጵያ የዘፈቀደ እሥራትና የሥቃይ አያያዝ የሚፈፀሙባት ሃገር” መሆኗን የሆርን ፅሁፍ ይጠቁምና “በተቃዋሚ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው ላይ ተካሄደ” ካለው አፈና በኋላ ገዥው ፓርቲ የፓርላማውን መቀመጫ ሙሉ በሙሉ መያዙን ያስታውሣል፡፡

በአብዛኛው ሰላማዊ እንደነበሩ ሂዩማን ራይትስ ዋች በገለፃቸው ኦሮምያ ውስጥ በተካሄዱ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ወቅት የመንግሥቱ የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅመው የሚበልጡት ተማሪዎች የሆኑ አራት መቶ ሰዎችን መግደላቸውን፤ ሺኾች መታሠራቸውን በቅርቡ ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት ማብራራቱን ሆርን አብራርቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት የመንግሥቱ ኃይሎች በኦሮምያ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወቅት የወሰዱት እርምጃ ተገቢና ተመጣጣኝ እንደነበረ ተናግሯል፡፡

የተገደሉ ሰዎች ቁጥርም 173 እንደሆነ አመልክቶ 14 የፀጥታ ኃይል አባላት መሆናቸውን አስረድቷል፡፡

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት ዓለምአቀፍ ደረጃዎችን የማይጠብቅ ነው ሲል የሚያጣጥለው የሂዩማን ራይትስ ዋች መርማሪ በግድያዎቹ ላይ ነፃና ተዓማኒነት ያለው ምርመራ ዓለምአቀፍ ድጋፍ ታክሎበት እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሂዩማን ራይትስ ዋች ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር አክሻያ ኩማር በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያን ለሁለት ዓመታት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ተለዋጭ አባል ሆና መመረጥ የሚያዩት ለመልካም ተግባር ከሚሰጥ ሽልማት ይልቅ እንደፖለቲካ ድርጎ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የኢትዮጵያን መመረጥ ተከትሎ ከኒው ዮርክ ባስተላለፉት የደስታ መግለጫ መልዕክታቸው ኢትዮጰያ የዓለምን ዕምነትና ክብር ተጎናፅፋለች ማለታቸውን ሱዳን ትሪብዩን ዘግቧል፡፡

ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

የሂዩማን ራይትስ ዋች ባለሙያዎች ስለኢትዮጵያ ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት መመረጥ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:51 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

XS
SM
MD
LG