በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለኢትዮጵያ የግጭት ሰለባዎች ፍትሕ በመንግሥት ላይ ግፊት እንዲደረግ ሂውማን ራይትስ ዎች ጠየቀ


በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ በትግራይ አቢ አዲ በሚገኝ መጠለያ፣ አቢ አዲ፤ ትግራይ ክልል እአአ ሰኔ 20/2023
በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ በትግራይ አቢ አዲ በሚገኝ መጠለያ፣ አቢ አዲ፤ ትግራይ ክልል እአአ ሰኔ 20/2023

በሰሜን ኢትዮጵያ፣ ለሁለት ዓመታት የተደረገውን ጦርነት ያቆመው የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ አንድ ዓመት ቢኾነውም፣ ውጊያ እና ከፍተኛ የመብቶች ጥሰት አሁንም ቀጥሏል፤ ሲል፣ ሂውማን ራይትስ ዎች ዛሬ አስታውቋል።

በጦርነቱ ላይ የነበሩት የፌዴራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች፣ በአፍሪካ ኅብረት ሸምጋይነት በደቡብ አፍሪካ-ፕሪቶርያ ላይ የሰላም ስምምነቱን የፈረሙት ከዓመት በፊት ነበር፡፡

“የኢትዮጵያ መንግሥት እና ዓለም አቀፍ አጋሮቹ፣ ባለፈው አንድ ዓመት ታይቷል ያሉትን መሻሻል ቢያወድሱም፣ በግጭት አካባቢ ያሉ ሲቪሎች፣ አሁንም ሁከት እየተፈጸመባቸው ነው። በሌሎች የአገሪቱ ክልሎችም ውጊያ ቀጥሏል። ከዚኽ በፊት ጥሰት የፈጸሙ አካላትም፣ ያለ ተጠያቂነት ድርጊቱን ቀጥለዋል፤” ሲሉ፣ የሂውማን ራይትስ ዎች አፍሪካ ዲሬክተር ላቲሻ ቤደር እንደተናገሩ፣ መግለጫው ጠቅሷል።

ስምምነቱ ክፍተቶች እንደነበሩት የጠቀሰው የሰብአዊ መብቶች ቡድኑ፣ ተዋጊ ኀይሎች፣ በትግራይ ክልል የሰብአዊ መብቶች ጥሰታቸውን ቀጥለዋል፤ ብሏል።

የኤርትራ ኀይሎች፥ የጾታ ጥቃት፣ እገታ እና ዘረፋ እንደፈጸሙ፤ የሰብአዊ ርዳታ እንዳይደርስ እንዳስተጓጎሉ፣ እንዲሁም ኀይሎቹ በሚቆጣጠሯቸው ቦታዎች የአፍሪካ ኅብረት ተቆጣጣሪዎች ሥራ እንዳይሠሩ ዕንቅፋት እንደፈጠሩ፣ ሂውማን ራይትስ ዎች አስታውቋል።

ድርጅቱ፣ “ምዕራብ ትግራይ” ብሎ በጠራው፣ ነገር ግን የዐማራው ወገን የባለቤትነት ጥያቄ በሚያነሣበት አካባቢ፣ ባለሥልጣናት እንዲሁም የዐማራ ክልል ኀይሎች እና የፋኖ ሚሊሺያ “የዘር ማጽዳት” ያለውን “ዘመቻ” እንደቀጠሉና “የትግራይ ተወላጆችንም በኀይል እያስወጡ” እንደኾነ ገልጿል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፕሮግራም፣ የርዳታ እህል ዘረፋ እንደተካሔደ በመግለጽ፣ ባለፈው መጋቢት ለትግራይ የሚሰጡትን የምግብ ዕደላ ማቆማቸው፣ እንዲሁም በግንቦት ወር ደግሞ፣ በመላ ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የርዳታ ሥርጭት ማቆማቸው፣ ወትሮውንም ስቃይ ላይ በነበረው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፤ ብሏል።

በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ሚሊሺያዎች መካከል፣ ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ ውጊያው እንደተባባሰ ያወሳው ድርጅቱ፣ በመቶ የሚቆጠሩ ሲቪሎች እንደተገደሉ፣ የዐማራ ተወላጆች በጅምላ እንደታሰሩ፣ የሲቪል መሠረተ ልማቶች እንደወደሙ የደረሱት ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱ ጠቁሟል።

ባለሥልጣናት ወደ ቀድሞው የመጨቆኛ ዘዴያቸው ተመልሰዋል፤ ያለው ድርጅቱ፣ መረጃ በወቅቱ እንዳይደርስ ማገዳቸውን፤ ገለልተኛ የኾነ ማጣራት እንዳይኖር ማድረጋቸውን፤ በተጨማሪም፣ በክልሉ ባለፈው ነሐሴ ኢንተርኔት ማቋረጣቸውንና ከፍተኛ ውጊያ ባለባቸው አካባቢዎች ያለው የስልክ አገልግሎትም እያለፈ ካልኾነ በቀር እንደማይገለግል፣ ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ባለፈው ነሐሴ፣ በዐማራ ክልል እስከ ስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ማወጁንና ክልሉን በወታደራዊ ዕዝ ሥር እንዲተዳደር ማድረጉን እንዲሁም፣ በዐዋጁ መሠረት ተጠርጣሪ የተባሉ ሰዎች ያለፍ/ቤት ፈቃድ እንደሚያዙ፣ የሰዓት እላፊ እንደታወጀ፣ መሰብሰብ እንደተከለከለ፣ የሰዎች መኖሪያ ያለሕግ እንደሚፈተሽ ድርጅቱ አትቷል።

በሰሜን ጎንደር የምትኖር የ24 ዓመት ሴት፣ “ሰዎች ይገደለሉ፤ ይያዛሉ። ነገሮች ይበልጥ ተበላሽተዋል። ደኅንነት አይሰማኝም። ማንም ሰው ደኅንነት አይሰማዉም፤” ማለቷንም ጠቅሷል።

በተመድ የተቋቋመው የሰብአዊ መብቶች ባለሞያዎች ቡድን፣ ለሁለት ዓመታት በተካሔደው ጦርነት ከፍተኛ ጥሰት እንደተፈጸመ መግለጹንና አሁንም ከፍተኛ ሠቆቃ የመድረስ ዕድሉ ከፍተኛ እንደኾነ፣ ከሰላም ስምምነቱም በኋላ፣ ሁከት እና የመብቶች ጥሰት በመላ አገሪቱ እንደቀጠለ ማስታወቁን፣ የመብቶች ድርጅቱ መግለጫ አመልክቷል።

ቀጣይ ገለልተኛ ምርመራዎች እና ዓለም አቀፍ ቁጥጥር እንደሚያስፈልግ ግልጽ ቢኾንም፣ የተመድ የሰብአዊ ም/ቤት አባል ሀገራቱ፣ የባለሞያዎቹን ቡድን የሥራ ዘመን ሳያራዝሙ እንደቀሩ አስታውሷል። ውሳኔው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የቡድኑ ሥራ እንዳይቀጥል ባደረገው ከፍተኛ የማግባባት ዘመቻ እና ቡድኑ ሥራውን እንዲያቆም የሚጠይቅ የውሳኔ ሐሳብ ለም/ቤቱ እንደሚያቀርብ መዛቱን ተከትሎ የተላለፈ እንደነበር፣ ሂውማን ራይትስ ዎች አስታውሷል።

ካለፈው መጋቢት ጀምሮ፣ የሽግግር ፍትሕን አስመልክቶ ምክክር እየተደረገ መኾኑን መንግሥት ቢያስታውቅም፣ በሕግ የተጠየቁት ሰዎች ጥቂቶች እንደኾኑና የመብቶች ጥሰት የተካሔደባቸው ሰዎች፣ በሒደቱ ላይ እምነት እንደሌላቸው፣ ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጿል። ስለዚኽም፣ ተመድ እና የሚመለከታቸው መንግሥታት፣ በኢትዮጵያ የግጭት ሰለባዎች ፍትሕ ያገኙ ዘንድ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው፣ ድርጅቱ አመልክቷል።

“ደካማ የኾነውን የሰላም ስምምነቱን አፈጻጸም የሚደግፉ መንግሥታት፣ በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን ቀውስ እንዳላየ መኾን አይችሉም። በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ሰለባዎች፣ ተደጋጋሚ በደል የሚፈጸምበትና የሕግ ተጠያቂነት የሌለበት የወደፊት ሕይወት አያሻቸውም፤” ሲሉ፣ የሂውማን ራይትስ ዎች አፍሪካ ዲሬክተር ላቲሻ ቤደር ማሳሰባቸውን መግለጫው አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG