በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ንግድ ባንክ አላግባብ ገንዘብ ወስደዋል ላላቸው ተጨማሪ ቀነ ገደብ አስቀመጠ


ንግድ ባንክ አላግባብ ገንዘብ ወስደዋል ላላቸው ተጨማሪ ቀነ ገደብ አስቀመጠ
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:54 0:00

ንግድ ባንክ አላግባብ ገንዘብ ወስደዋል ላላቸ ተጨማሪ ቀነ ገደብ አስቀመጠ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከ12 ቀናት በፊት ያጋጠመውን የሥርዐት ችግር ተከትሎ፣ አላግባብ ገንዘብ ወስደዋል ያላቸው፣ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ያልመለሱ የ5ሺሕ731 ሰዎችን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲኾን፣ እንዲመልሱም ተጨማሪ ቀነ ገደብ ማስቀመጡን አስታውቋል፡፡

ባንኩ ባወጣው መግለጫ፣ በስም ዝርዝር የተገለጹት ሰዎች የወሰዱትን ገንዘብ እስከ መጪው ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ድረስ እንዲመልሱ አሳስቧል፡፡ ቀነ ገደቡን አክብረው ገንዘቡን በሚመልሱት ሰዎች ላይ፣ በቀጣይ የሚወሰድ ሕጋዊ ርምጃ እንደማይኖርም አረጋግጧል፡፡

ባንኩ፣ የሥርዓት ችግሩ ከተከሠተ በኋላ፣ አላግባብ ገንዘብ ያወጡ ሰዎች እንዲመልሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው ቀነ ገደብ፣ ከ14ሺሕ400 በላይ ግለሰቦች የወሰዱትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መመለሳቸውን አስታውቋል፡፡

ትላንት ማክሰኞ፥ ስማቸውን፣ የሒሳብ ቁጥራቸውንና ሒሳባቸው የተከፈተበትን ቅርንጫፍ ይፋ ያደረገው ባንኩ፣ ወስደዋል የተባሉትን ገንዘብ በሙሉ ያልመለሱ 565 ግለሰቦች እና በከፊል ተመላሽ አድርገዋል የተባሉ 5ሺሕ166 ግለሰቦች፣ ገንዘቡን በተሰጠው ቀነ ገደብ እንዲመልሱ አሳስቧቸዋል፡፡

በተሰጠው ቀነ ገደብ ውስጥ ገንዘቡን ተመላሽ ካላደረጉ ግን፣ የተለያዩ የብዙኀን መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ሙሉ ስማቸውንና ፎቷቸውን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግና በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ በመውሰድ ወንጀል እንዲጠየቁ ለሚመለከታቸው የሕግ አካላት እና ተቋማት እንደሚያሳውቅ አስጠንቅቋል፡፡ ከእነኚህ ተቋማት ጋራ በመተባበርም፣ ቀጣይ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር እና የአስተዳደር ሕጋዊ ርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው እንደሚያደርግ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከ12 ቀናት በፊት ያጋጠመውን የሥርዐት ችግር ተከትሎ፣ ከተወሰደበት ገንዘብ ውስጥ እስከ አሁን 80 ከመቶውን ማስመለሱን፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምሕረቱ ትላንት ማክሰኞ ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ብሔራዊ ባንክ ሙሉ ምርመራ እያካሔደ እንደሚገኝ አቶ ማሞ ጠቁመው፣ ግኝቱን የሚመለከት ሪፖርትም ከሳምንት በኋላ እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ትላንት በሰጠው መግለጫው፣ ባጋጠመው የሥርዓት ችግር ምክንያት ከ801ሚሊዮን 400 ሺሕ በላይ የሚኾን ብር አላግባብ እንደተወሰደበት አስታውቆ፣ እስከ አሁን 622ነጥብ9 ሚሊዮኑን እንዳስመለሰ ገልጿል፡፡

እንደ መግለጫው፣ ችግሩ በተከሠተበት ዕለት፣ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ከ38 ደቂቃ ጀምሮ በነበሩት የአምስት ሰዓታት ጊዜ ውስጥ፣ ከ238ሺሕ በላይ ሕገ ወጥ የገንዘብ ግብይቶች ተከናውነዋል፡፡ እስከ አሁን ድረስም፣ በድርጊቱ የተሳተፉ 9ሺሕ281 ግለሰቦች የወሰዱትን ገንዘብ በሙሉ መመለሳቸውን ባንኩ አስታውቋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG