የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከ12 ቀናት በፊት ያጋጠመውን የሥርዐት ችግር ተከትሎ፣ አላግባብ ገንዘብ ወስደዋል ያላቸው፣ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል ያልመለሱ የ5ሺሕ731 ሰዎችን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲኾን፣ እንዲመልሱም ተጨማሪ ቀነ ገደብ ማስቀመጡን አስታውቋል፡፡
ባንኩ ባወጣው መግለጫ፣ በስም ዝርዝር የተገለጹት ሰዎች የወሰዱትን ገንዘብ እስከ መጪው ቅዳሜ መጋቢት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ድረስ እንዲመልሱ አሳስቧል፡፡ ቀነ ገደቡን አክብረው ገንዘቡን በሚመልሱት ሰዎች ላይ፣ በቀጣይ የሚወሰድ ሕጋዊ ርምጃ እንደማይኖርም አረጋግጧል፡፡
ባንኩ፣ የሥርዓት ችግሩ ከተከሠተ በኋላ፣ አላግባብ ገንዘብ ያወጡ ሰዎች እንዲመልሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጠው ቀነ ገደብ፣ ከ14ሺሕ400 በላይ ግለሰቦች የወሰዱትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መመለሳቸውን አስታውቋል፡፡
ትላንት ማክሰኞ፥ ስማቸውን፣ የሒሳብ ቁጥራቸውንና ሒሳባቸው የተከፈተበትን ቅርንጫፍ ይፋ ያደረገው ባንኩ፣ ወስደዋል የተባሉትን ገንዘብ በሙሉ ያልመለሱ 565 ግለሰቦች እና በከፊል ተመላሽ አድርገዋል የተባሉ 5ሺሕ166 ግለሰቦች፣ ገንዘቡን በተሰጠው ቀነ ገደብ እንዲመልሱ አሳስቧቸዋል፡፡