በዘንድሮው ድርቅ ምክንያት የደረሰው የምግብ እጥረት በምንም ዓይነት ከ1975ቱ ጋር የሚመሳሰል አይደለም ሲል ለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል፡፡
ኤምባሲው ትናንት ባወጣው መግለጫው በተጨባጭ ያለው ሁኔታ ምዕራባዊያን የዜና አውታሮች እያወጡ ካሏቸው ዘገባዎች ጋር ተቃራኒ ነው ብሏል፡፡
ቢቢሲ በሚል የእንግሊዝኛ መጠሪያ ስሙ ምኅፃር የሚታወቀው የእንግሊዝ የዜና ማሠራጫ አውታር ሰሞኑን ባወጣው አንድ የቴሌቪዥን ሪፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም ወሎ - ቆቦ አካባቢ ዘንድሮ የደረሰ ድርቅ የከበደ ረሃብ ማስከተሉን ዘግቧል፡፡
ሪፖርተሩ በቆቦ በተለይ ደግሞ የአደጋው ማዕከል ነው ባለው “ቀዩ ጋራ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተገኝቶ ከሥፍራው የዘገበ ሲሆን እንዲያውም ሰሞኑን በረሃብ ምክንያት ሞተ ባለው አብዱ መሃመድ በሚባል የአምስት ዓመት ሕፃን መቃብር ላይ መገኘቱን አሳይቷል፡፡
ዘጋቢው አክሎም በአንድ አካባቢ በቀን ሁለት ሕፃናት እየሞቱ መሆናቸውንና በመጭው የአውሮፓ ዓመት /በ2016 ዓ.ም/ በኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ የሚፈልገው ቁጥር ከ15 ሚሊየን እንደሚበልጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀም አመልክቷል፡፡
ሪፖርተሩ በቀዩ ጋራ አካባቢ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል አንደኛው የረሃቡ ሁኔታ ገና ጅምር ላይ ያለ ቢሆንም ወደፊት እየገፋ ይሄዳል ብለው እንደሚሰጉ ጠቁመው አደጋውን ከ1977ቱ ድርቅ ጋር አመሳስለውታል፡፡
ለንደን የሚገኘው በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትናንት፣ ጥቅምት 30/2008 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በዚህ የኤል ኒኞ ዓመት ምግብ በማጣት ማንም እንዳይሞት ለማድረግ መንግሥት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
“ምዕራባዊያን የዜና አውታሮች ከሚያወጧቸው ዘገባዎች ጋር በሚፃረር ሁኔታ እንኳን የ1977ቱን ሊያክል ቀርቶ ማንኛውንም ረሃብ የሚባልን ሁኔታ የሚመስል ክስተት አይኖርም” ብሏል መግለጫው፡፡
የኤምባሲው መግለጫ አክሎም “… በቢቢሲ ቴሌቪዥን የተላለፈው ሕፃናት በየዕለቱ እንደሚሞቱ የሚናገረው ዘገባ አሁን ያለውን ሰፊ እውነታና ችግሩን ለመጋፈጥም የተደረገውን ዝግጅት የማያሳይና የተጋነነ ነው” ብሎታል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
ለቢቢሲ ዘገባ ይህንን ፋይል ተጭነው ይከተሉ፡፡ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጥቅምት 30/2008 ዓ.ም ያወጣው የፕሬስ መግለጫ ሙሉ ቃል በእንግሊዝኛ ይህንን ፋይል በመጫን ለማንበብ ይችላሉ።