ዋሺንግተን ዲሲ - አዲስ አበባ —
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መደረጉን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቀ።
በክልልሉ ዛሬ በተደራጀ ሁኔታ በመንግሥት መዋቅር ላይ ጥቃት ለመሠንዘር መሞከሩን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅሕፈት ቤት የፕሬስ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ማምሻውን ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
የፌደራሉ መንግሥት ኃይሎች የባህርዳር ከተማንና አካባቢዋን ጨምሮ የክልሉን ደኅንነት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አቶ ንጉሡ ገልፀዋል።
አቶ ንጉሡ አክለውም በአድራጎቱ ውስጥ ተሣትፈዋል በሚባሉት ላይ “እርምጃ” ለመውሰድ ትዕዛዝ መሰጠቱን አመልክተው የክልሉም ሆነ የሐገሪቱ ሕዝብ ሰላሙን እንዲጠብቅ ጥሪ አድርገዋል።
ባሕር ዳር የምትገኘው ሪፖርተራችን ከተማዪቱ ውስጥ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበረ አረጋግጣልናለች።
“የተደራጁና የታጠቁ ናቸው” የተባሉትን ማንነትና የደረሰ ጉዳት ስለመኖር አለመኖሩም አቶ ንጉሡ ከመግለፅ ተቆጥበዋል።
ሁኔታዎችን ለማጣራት በየአቅጣጫው እያደረግን ያለነውን ሙከራ አካትተን የተሟላ መረጃ ለማድረስ ክትትል ላይ ነን፤ በደረሰ ጊዜ እናቀርባለን።
ከአቶ ንጉሡ ጥላሁን ጋር ያደረግነውን አጭር ቃለ-ምልልስ ከተያያዘው አጭር ቃለ-ምልልስ ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ