የአልማህዲ ጥፋትና የሚጠብቀው የፍርድ ቅጣት በአስተርጓሚ በተነበበት ጊዜ፤ በእስልምና እምነት ተከታይ ሰዎች ተገፋፍቶ ድርጊቱን እንደፈፀመ ገልጾ ሌሎች ሙስሊሞች የሱን ዱካ እንዳይከተሉም አሳስቧል።
ችሎቱ በአለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት እየቀረበ ያለው የእስልምና አክራሪው አህመድ አልፋቂ አልማህዲ ክስ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ቀርተውታል። አልማህዲ እ.አ.አ 2012 በሚላ ከተማ ቲምቡክቱ የሚገኙትን ታሪካዊ ሃውልቶችና መስጊዶች በማውደሙ ለተከፈተበት ክስ ጥፋተኛ መሆኑን በማመኑ ፍርድ ቤቱ ውሳኔው በጥቂት ቀናት ውስጥ ያሰማል።
የአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ዋና አቃቤ ህግ ፋቱ ቤንሶዳ የቲምቡክቱ የባህል ቅርሶችን ላይ የደረሰው ውድመት በሰብዓዊነት ላይ እንደተቃጣ ጥቃት ይቆጠራል በማለት ተናግረዋል።
"ባህል ማንነታችን ነው። ከኛ የቀደሙት ስዕሎችን፣ ቅርፃቅርጾችን፣ ሃውልቶችን፣ ታላላቅ ግንቦችንና ሌሎችም ባህላችንን የሚያንፀባርቁ ስራዎቻቸውን ትተውልን አልፈዋል። ልባቸውንና ነፍሳቸውን በነዚህ የፈጠራ ስራዎቻቸው ላይ አስቀምጠዋል። በጊዜያቸው የነበረውን የባህልና እምነት ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላለፉበትም ነው።" ፋቱ ቤንሶዳ