በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጋዜጠኛ እክስንድርና የአቶ አንዷለም ቤተሰቦች በሰሙት ዜና መደሰታቸውን ገለፁ


 አቶ አንዷለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
አቶ አንዷለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና አቶ አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ 746 እስረኞች በይቅርታና ክሳቸው ተቋርጦ እንዲለቀቁ መወሰኑ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ሰርካለም ፋሲል፤ ዜናውን ከሰማች በኋላ በጣም መደሰቷን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግራለች። የአቶ አንዷለም አራጌ ባለቤት ዶ/ር ሰላም አስቻለው በበኩሏ ካየች ብኋላ እንደምታረጋግጥ ተናግራለች።

የጋዜጠኛ እክስንድርና የአቶ አንዷለም ቤተሰቦች በሰሙት ዜና መደሰታቸውን ገለፁ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:05 0:00

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉን ጠቅሰው በዛሬው ዕለት እንደዘገቡት፤ እስረኞቹ ክሳቸው ተቋርጦና በይቅርታ ሲሆን የሚፈቱ ሲሆን በይቅርታ ቦርድ የተወሰነላቸው እስረኞች ጉዳያቸው ሀገሪቱ ርእሰ ብሔር ቀርቦ ሲጸድቅና የተሀድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ይለቀቃሉ ተብሏል።

ይፈታሉ የተባሉት እስረኞች 417 ፍርደኛ የነበሩና 329 ተጠርጣሪዎች ደግሞ ክሳቸው እንዲቋረጥ የተወሰነ ነው። ክሳቸው እንዲቋረጥ ከተወሰነላቸው ውስጥ 278 ከፌዴራል፣18 ከአማራ ክልልና 33 ከትግራይ ክልል መሆናቸው ተዘርዝሯል።

ከእነዚህ ውስጥ በስም የተጠቀሱት ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና የቀድሞው የአንድነት ለዴሞክራሲ እና ፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አንዷለም አራጌ ብቻ ናቸው። ሁለቱም መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም መታሰራቸው የሚታወስ ሲሆን ጋዜጠኛ እስክንድር 18 ዓመት አቶ አንዷለም አራጌ ደግሞ ዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ቃሊቲ በሚገኘው የፌደራል ማረሚያ ቤት ከታሰሩ ስድስት ዓመት ከስድስት ወራት ሆኗቸዋል። የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ሰርካለም ፋሲል፤ ዜናውን ከሰማች በኋላ በጣም መደሰቷን እና መደንገጧን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግራለች።

በዜናው በጣም ነው የተደሰትኩት ትልቁ ደስታዬ ደግሞ ለልጃችን ናፍቆት ነው።
የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ባለቤት ሰርካለም ፋሲል

“ በዜናው በጣም ነው የተደሰትኩት ትልቁ ደስታዬ ደግሞ ለልጃችን ናፍቆት ነው። ከዚህ በላይ ዝርዝር መናገር ይቅርብኝ። ምክኒያቱም ቀሪውን የእስክንድርን ድምፅ ከሰማሁ በኋላ ይሻለኛል። በአጠቃላይ የምለው ግን ቀሪዎቹ በአስተሳሰባቸውና በአመለካከታቸው የታሠሩ ሁሉም የሕሊና እስረኞች ተፈተው አንድ ዐይነት ደስታ የምንደሰትበት ጊዜ እንዲያደርግልን ነው ” ብላናለች።

ሰርካለም ዜናውን ከሰማች በኋላ ወደ ቤተሰቦቿ ስልክ ደውላ ሁኔታውን ለማጣራት እንደሞከረች ገልፃ እነሱም ዜናውን ከመስማታቸው ውጪ አዲስ ነገር እንዳልሰሙ ገልፃልናለች።

የአቶ አንዷለም አራጌ ባለቤት ዶ/ር ሰላም አስቻለውም በተመሳሳይ እሁድ ዕለት ገብታ ስትጠይቀውም ሆነ ዛሬም ጠያቂ በገባለት ጊዜ እርሱም ሆነ ቤተሰቦቹ ምንም ዐይነት ፍንጭ እንዳልነበራቸው ገልፃ ዜናውን ከሰው እንደሰማች ጠቁማናለች።

ስሙ ተጠርቷል ብለው ነው በደንብ አስረግጠው የነገሩኝ። እኔ ግን ከሰማሁ ወይም ካየሁ በኋላ ነው የማረጋግጠው
የአቶ አንዷለም አራጌ ባለቤት ዶ/ር ሰላም አስቻለው

አያይዛም “ዜናውን አላዳመጥኩም ሰዎች ናቸው ደውለው የነገሩኝ። ስሙ ተጠርቷል ብለው ነው በደንብ አስረግጠው የነገሩኝ። እኔ ግን ከሰማሁ ወይም ካየሁ በኋላ ነው የማረጋግጠው” ብላለች።

ዶ/ር ሰላም አያይዛ የ10 እና አንድ የሰባት ዓመት ሁለት ልጆች እንዳሏቸው ገልፃ እርሱ ሲታሰር ሕፃናት ነበሩ መፈታቱ በተለይ ለእነሱ እጅግ ታላቅ ደስታ መሆኑን ገልፃልናለች።

ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ደህንነት ተሟጋች ቡድን /ሲፒጄ/ የአፍሪካ ቀንድ ተከራካሪ አንጄላ ኲንታል ዜናውን ከመንግሥት ሚዲያ ላይ መስማታቸውን ጠቅሰው ”እውነት ነው ብለን እናምናለን። ከደስታም በላይ የሆነ ዜና ነው” ካሉ በኋላ፤ “እስካሁን ወደ ሰባት ዓመት በእስር ቆይቷል። በኛ እይታ እነዚህ ሰባት ረጃጅም ዓመታት ናቸው። አንቺም ሆንሽ አድማጮችሽ እንደሚያውቁት የዐስራ ስምንት ዓመታት እስራት ነው የተፈረደበት። ይሄ ትልቅ የፍትህ መዛባት ነው የሚል እምነት አለን። አሁን ከእስር ወጥቶ ነፃ ከሆነ… እርግጥ ነው ዜናው ትክክል ነው የሚል ተስፋ አለኝ። ከሆነም ልንደሰትበት የሚገባ ጉዳይ ነው።” ብለውናል።

ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢስት አፍሪካ ሪጅናል ምክትል ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን፤ በዛሬው ዕለት ባወጡት አጭር መግለጫ፤ አንድ ቀን እንኳን በእስር ማሳለፍ የማይገባው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ሥራውን በመሥራቱ ብቻ ሰባት ዓመት በእስር አሳልፏል። ከእስር ወጥቶ ነጻ መሆኑ ግሩም ዜና ነው። ብለዋል።

አያይዘውም እንደ አቶ በቀለ ገርባ፣አዲሱ ቡላና ውብሸት ታዬ ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ሊፈቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሰፋ ያለ ማብራሪያ ለማግኘው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ የእጅ ስልክ ላይ ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገን ስልካቸው አይነሳም። በመጨረሻም ባህር ዳር ስብሰባ ላይ መሆናቸው ተነግሮናል። በተጨማሪም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮን ለማግኘት ሞክረንም አልተሳካልንም።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መረጃ፤ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የይቅርታና የክስ ማቋረጥ እንደሚያደርግ በወሰነው መሰረት የተከናወነ ነው እንደሆነ አስታውቋል።

ከዚህ ውሳኔ በኋላ ታዋቂውን ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራን ጨምሮ የተወሰኑ እስረኞች መፈታታቸው የሚታወስ ሲሆን በሀገር ውስጥ የእስረኞችን ጉዳይ የሚከታተሉ ተሟጋቾችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የኅሊናና የፖለቲካ እስረኞች መኖራቸውን በመግለፅ ሁሉም እንዲፈቱ ሲጠይቁ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG