ቬንዙዌላቷ ጸሐፊና ጋዜጠኛ ሚላግሮስ ሶኮሮ ሽልማቱን ለመቀበል በነገው ዕለት ኔዘርላንድ ትገኛለች። “ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ግን እስር ቤት በመሆኑ በዕለቱ መታደም አይችልም” ሲሉ የኦክስፋም ኖቪብ ዳይሬክተር ፋራህ ካሪሚ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
ፋራህ ካሪሚ ስለ ሽልማቱ ሲናገሩ “እስክንድር ነጋ ለረጅም ጊዜ ለመናገር ነፃነት የታገለ በጣም የተከበረ ጋዜጠኛ ነው። ይሄ ሽልማት፤ ለማኅበረሰባቸው ፍትሕ፣ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ ለአካባቢ ጥበቃና ለመሳሰሉት መብቶች በሥራቸው ሲታገሉና ጮክ ብለው ስለተናገሩ እስር የደረሰባቸውን ጋዜጠኞችና ጸሐፊዎችን ለማበረታታት የሚሰጥ ሽልማት ነው።”ብለዋል።
አያይዘው “እንዳለመታደል ሆኖ እስክንድር እስር ቤት በመሆኑ ምክኒያት ነገ ምሽት እዚህ ተገኝቶ ሽልማቱን መቀበል አይችልም። ዋናው የሽልማቱ አላማ በሞያው ለከፈለው ዋጋ እውቅና መስጠት ነው። ያም ሆኖ ጥቂት የገንዘብ ሽልማት አለው። ይህም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኘው ለእርሱና ለቤተሰቡ ጥቂት እገዛን ያደርጋል የሚል ተስፋ አለን”ብለዋል።
ከሽልማቱ ጎን ለጎን ከእስር የመለቀቁ ሁኔታም እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል “ዛሬ ባገነኘው መረጃ የኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰኑ እስረኞችን መፍታቱን ሰምተናል። በቀጣይም እስክንድር ነጋንና ሌሎች ሁሉንም ቀሪ እስረኞች መንግስቱ ይፈታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ዳይሬክተሯ የተናገሩት ነው።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ