ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ቀድሞ የታገዱ ድርጅቶቹ አቤቱታ እንደደረሰው ገልጾ ጉዳዩን እየተከታተለ ባለበት ወቅት “ተመሳሳይ ይዘት ባለው እና ተቋማቱ የፈጸሟቸውን ከባድ የሕግ ጥሰቶች በዝርዝር ባላስቀመጠ ደብዳቤ“ ተጨማሪ ሁለት ድርጅቶች መታገዳቸውን አሳሳቢ ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል፡፡
በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ በተደጋጋሚ የሚተላለፉ እገዳዎች የሲቪክ ምኅዳሩን በማጥበብ እና በማኅበር የመደራጀት መብት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይፈጥሩ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ሲልም አሳስቧል፡፡
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በአሁኑ ወቅት በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የሚሠሩትን የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማእከል፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከልን ከማንኛውም እንቅስቃሴ አግዷል፡፡
ባለሥልጣኑ፣ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶችን ያገደው “ገለልተኛ አይደላችሁም፣ ከዓላማ ውጭም ተንቀሳቅሳችኋል” በሚል እና ተያያዥ ምክንያቶች መኾኑን በጻፈላቸው ደብዳቤ አመልክቷል፡፡
የታገዱ ድርጅቶች ኅላፊዎችም የቀረበበባቸውን ውንጀላ ለአሜሪካ ድምጽ በሰጧቸው አስተያየቶች ማስተባበላቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም “ባለሥልጣኑ የድርጅቶቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ የምርመራ ሥራዎቹን በተቻለ ፍጥነት አጠናቆ ወደ ሥራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ እንዲያመቻች” በመግለጫው ጠይቋል፡፡
መድረክ / ፎረም