በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፍርድ ቤት በእነቀሲስ በላይ መኰንን ላይ የክስ መመሥረቻ የ15 ቀን ጊዜ ሰጠ


ፍርድ ቤት በእነቀሲስ በላይ መኰንን ላይ የክስ መመሥረቻ የ15 ቀን ጊዜ ሰጠ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:17 0:00

ፍርድ ቤት በእነቀሲስ በላይ መኰንን ላይ የክስ መመሥረቻ የ15 ቀን ጊዜ ሰጠ

ዐቃቤ ሕግ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ክስ ለመመሥረት የጠየቀው የ15 ቀን ጊዜ ተፈቅዶለታል፡፡

ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንንን ጨምሮ፣ ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ከስድስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማውጣት ሙከራ በማድረግ የተጠረጠሩት ሦስት ግለሰቦች፣ ዛሬ ኀሙስ፣ ለሦስተኛ ጊዜ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ክርክር ተደርጓል፡፡

ዐቃቤ ሕግ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይንና አብረዋቸው የታሰሩ ሁለት ግለሰቦችን፣ በከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠሩን ለችሎቱ ገልጿል፡፡

የተጠርጣሪዎች ጠበቆች በበኩላቸው፣ ዐቃቤ ሕግ ተጨማሪ ጊዜ ሳያስፈልገው ክስ መሥርቶ መቅረብ እንደነበረበት ገልጸው፣ ደንበኞቻቸው በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

የዛሬው ችሎት የተቀጠረው፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን፣ እንዲሁም ያሬድ ፍሥሓ እና ዳባ ገናና በተባሉ ሹፌራቸው እና አጃቢያቸው ላይ ምርመራ ለማጣራት፣ ፖሊስ ለሁለተኛ ጊዜ በፍርድ ቤቱ በተሰጡት ሰባት የምርመራ ቀናት ውስጥ ያከናወነውን ምርመራ ለመመልከት ነበር፡፡

መርማሪ ፖሊስ፣ ምርመራውን አጠናቆ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ መላኩን፣ በዛሬው ችሎት ላይ ገልጿል፡፡

መዝገቡ የደረሰው በዛሬው ዕለት እንደኾነ የገለጸው ዐቃቤ ሕግም፣ የክስ መመሥረቻ የ15 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ከተጠርጣሪ ጠበቆች ጋራ ክርክር ተደርጓል፡፡

ዐቃቤ ሕግ፣ የ15 ቀናት የክስ መመሥረቻ ጊዜ እንዲሰጠው የጠየቀው፣ ተጠርጣሪዎቹን በከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠሩንና ይህም ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ፣ ዋስትናም

የሚያስከለክል መኾኑን በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 109 መሠረት በመጥቀስ ነው፡፡

ይህን ተከትሎ ችሎት የቀረቡ ስድስት የተጠርጣሪ ጠበቆች ባነሡት ክርክር፣ ደንበኞቻችን ወንጀለኛ መኾናቸው ገና ባልተረጋገጠበት ኹኔታ ዋስትና ሊከለከሉ አይገባም፤ በማለት ተከራክረዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በምርመራ ወቅት ተሳትፎ እንዳለው ጠቅሰው፣ “ዐቃቤ ሕግ የሚያውቀውን መዝገብ ተመልክቶ ክስ ለመመሥረት ተጨማሪ የ15 ቀን ጊዜ አያስፈልገውም፤ ክሱን አዘጋጅቶ መቅረብ ነበረበት፤” ብለዋል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በምላሹ ባቀረበው መከራከሪያ ደግሞ፣ መሥሪያ ቤቱ በምርመራ ወቅት ለፖሊስ ድጋፍ ከማድረግ ያለፈ ተሳትፎ እንደሌለው በመጥቀስ፣ በመሸኛ ዛሬ ደረሰኝ ያለውን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ክስ የሚመሠርትበት ጊዜ እንደሚያስፈልገው አመልክቷል፡፡

ጠበቆች ባነሡት ሌላ መከራከሪያ፣ “ሐሰተኛ” በተባለው ሰነድ ላይ የሦስቱም ተጠርጣሪዎች ስም እንዳልተጠቀሰ ገልጸው፣ ይህም “በወንጀል የማያስጠረጥራቸው ነው” ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ የሃይማኖት አባት መኾናቸውን፣ የልማት ሥራ አስተባባሪ እና ቋሚ አድራሻ ያላቸው፣ ወደፊት ከተፈለጉ በማንኛውም ሰዓት ሊቀርቡ የሚችሉ መኾናቸውን በመጥቀስ፤ 2ኛ እና 3ኛ ተጠርጣሪዎች ደግሞ፣ በጉዳዩ ላይ ምንም ተሳትፎ የሌላቸው ናቸው፤ በማለት ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፣ ከ10 ዓመት በላይ ሊያስቀጣ በሚችል ከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠር ዋስትና የሚያስከለክል መኾኑ ሕጋዊ እና ሥነ ሥርዓታዊ ነው፤ ሲሉ ተከራክሯል። የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ዳኛ፣ ዐቃቤ ሕግ የጠየቀውን 15 ቀን የክሥ መመሥረቻ ጊዜ ፈቅደው ችሎት መልስ ኾኗል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ጉዳዩን በማስመልከት ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለው የኅብረቱ ሒሳብ፣ ስድስት ሚሊዮን ኀምሳ ሺሕ ዶላር ለማጭበርበር የተደረገው ሙከራ መክሸፉን አስታውቋል።

የአፍሪካ ኅብረት ተቀጣሪ ያልኾነ ግለሰብ፣ “ለግንባታ እና ለውኃ ቁፋሮ ሥራዎች በሚል የተጭበረበረ የክፍያ ትእዛዝ ገንዘቡን ከኅብረቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሒሳብ ለማውጣት ሞክሯል፤” ሲል አመልክቷል፡፡

"የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች እና የኅብረቱ የፋይናንስ ዲፓርትመንት፣ የማጭበርበር ሙከራውን በተሳካ ኹኔታ በማክሸፍ፣ ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ በማስወገድ” ወስደዋል ያለውን ፈጣን ርምጃ እንደሚያደንቅም ገልጿል፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው፣ ሚያዝያ 7 ቀን በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ቅጽር ባለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ መኾኑን ኅብረቱ ገልጾ፣ የኢትዮጵያ የጸጥታ አካላት ተጠርጣሪዎችን ለይተው ጉዳዩ በሕግ ሒደት ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG