በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ጆንሰን አፈጉባዔ ሆኑ


የሉዊዚያና ተወካይ ማይክ ጃንሰን
የሉዊዚያና ተወካይ ማይክ ጃንሰን

የታደሰ

በአመራር ላይ የበዛ ልምድ የላቸውም የተባሉት የሉዊዝያና እንደራሴ ጆንሰን ውዝግብ ከበዛባቸው የምርጫ ዙሮች በኋላ ነው ዛሬ 220 ለ209 በሆነ ድምፅ የተመረጡት።

የቀደሙት አፈጉባዔ ኬቭን ማካርቲ ከሥራቸው ከተነሱ ከመስከረም 22/2016 ዓ.ም. አንስቶ ላለፉት ሃያ ሁለት ቀናት በሪፐብሊካኑ አብላጫ መቀመጫ የተያዘው የተወካዮች ምክር ቤት ያለመሪና ያለሥራ ተሽመድምዶ ቆይቷል።

ምክር ቤቱ እሥራዔል ሃማስ ላይ፤ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለሚያካሂዷቸው ጦርነቶች መደገፊያ እንዲውል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የጠየቁትን የ106 ቢሊዮን ዶላር በጀት ተመልክቶ ድምፅ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በምክር ቤቱ ድምፅ ለመስጠት የተገኙ ሁሉም 209 የዲሞክራቲክ ዓባላት፣ ለፓርቲው ዕጩ ሃኪም ጀፈሪስ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።

በምክር ቤቱ ሪፖብሊካኖች 221 መቀመጫ ሲኖራቸው ዴሞክራቶች ደግሞ 212 መቀመጫ ይዘዋል፤ ሁለት መቀመጫዎች ደግሞ ክፍት ናቸው፡፡

ቀድሞ በዕጩነት ቀርበው የነበሩት ታም ኤመር ትናንት ከሰዓት በኋላ ከዕጩነት ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ፣ ማይክ ጃንሰን ማምሻውን ዕጩ ሆነ ተመርጠው ነበር።

ዛሬ ማለዳ ደግሞ፣ የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ ማይክ ጃንሰንን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

የሪፐብሊካኖቹ የውስጥ ሽኩቻ፣ የአፈ ጉባኤውን ቦታ ለሦስት ሳምንታት ክፍት እንዲሆን አድርጓል።

ምክር ቤቱ እስከ ህዳር 7 ድረስ በጀት እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል። ሥምምነት ላይ የማይደረስ ከሆነ፣ የመንግስት ሥራ በከፊል እንደሚዘጋ ተነግሯል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም ከዋይት ሃውስ የቀረበውንና 61 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን፣ እንዲሁም 14 ቢሊዮን ዶላር ለእስራኤል እንዲሠጥ የቀረበውን ጥያቄ ይመለከታል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG