በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሪፐብሊካኖች ዕጩ አፈጉባኤ መረጡ


የሉዊዚያና ተወካይ ማይክ ጃንሰን
የሉዊዚያና ተወካይ ማይክ ጃንሰን

ላለፉት ሦስት ሳምንታት፣ የምክር ቤት አፈጉባኤን ለመምረጥ ያልቻሉት የአሜሪካ ተወካዮች ም/ቤት የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት፣ ትላንት ማክሰኞ ማምሻውን፣ በአንድ ዕጩ ላይ እንደተስማሙ ተነግሯል።

ሪፐብሊካኖቹ በዝግ ባደረጉት ስብሰባ፣ የሉዊዚያናውን ተወካይ ማይክ ጃንሰን፣ ለአፈጉባኤነት ዕጩ ኾነው እንዲቀርቡ ተስማምተዋል። የቀድሞው አፈ ጉባኤ ከቪን ማካርቲ ከተነሡ ወዲህ፣ ሪፐብሊካኖቹ በዕጩነት የተስማሙባቸው የመጀመሪያ ተወካይ ማይክ ጃንሰን ናቸው።

ጃንሰን፣ እ.አ.አ በ2020 ምርጫ ወቅት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ፣ ውጤቱን ለመገልበጥ በሞከሩበት ጊዜ፣ ሪፐብሊካኖች ከትረምፕ ጎን እንዲሰለፉ ሚና ተጫውተው እንደነበር ተወስቷል።

ትላንት ማምሻውን በተደረገው የዕጩዎች ምርጫ፣ ማይክ ጃንሰን 128 ድምፅ አግኝተዋል፤ ተብሏል። ዋናው ድምፅ በምክር ቤቱ በሚሰጥበት ወቅት፣ የአፈ ጉባኤውን መዶሻ ለመጨበጥ 217 ድምፅ ያስፈልጋቸዋል። የአብዛኛውን ሪፐብሊካን ተወካዮች ድምፅ ያገኙ እንደኹ፣ እስከ አሁን ግልጽ አይደለም።

ላለፉት ሦስት ሳምንታት ያለ አፈጉባኤ የቆየው ምክር ቤቱ፣ በተለይም በበጀት ጉዳይ ላይ ለመወሰን አልተቻለም። እስከ መጪው ኅዳር 7 ቀን ድረስ፣ አፈ ጉባኤው ተመርጦ የበጀት ስምምነት ላይ ካልተደረሰ፣ የመንግሥት ሥራ በከፊል ሊዘጋ እንደሚችል ተመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG