በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የመንግስታቱ ድርጅት የኤርትራ መሪዎችን ጉዳይ ወደ አለምአቀፍ የወንጀሎች ፍርድቤት ይልክ ይሆን?


የተመድ የአጣሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ማይክ ስሚት
የተመድ የአጣሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ማይክ ስሚት

ማክሰኞለት የተባበሩት መንግስታት የመብት አጣሪ ቡድን የኤርትራ ባለስልጣናት በዜጎቻቸው ላይ እየፈጸሙ ነው ያላቸውን ሰፊ የመብት ጥሰቶች፤ አስረድቶ የኤርትራ መሪዎች በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ወይንም በሌሎች የፍትህ ችሎቶች ክስ እንዲመሰረትባቸው መጠየቁ ይታወሳል።

አጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ባቀረበባት ጂኒቫ የድጋፍና ተቃውሞ ሰልፎች ሰሞኑን ሲከናወኑ ቆይተዋል። የአፍሪካ ህብረት መቀመጫዋ አዲስ አበባና በትግራይ የስደተኞች ጣቢያ የሚኖሩ ኤርትራዊያን በዛሬውለት የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል። የኮሚሽኑን ሪፖርት በመቃወም ወደ 45ሽህ አቤቱታዎችም ተሰብስበዋል።

የኤርትራዊያን ሰልፍ በጄነቫ
የኤርትራዊያን ሰልፍ በጄነቫ

በዚህ ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኤርትራ ላይ የሰብዓዊ መብት ይዞታን እንዲመረምር የሰየመው አጣሪ ኮሚሽን የኤርትራ ባለስልጣናትና አስተዳድር በዜጎች ላይ ያደርሷቸዋል ያላቸውን ወንጀሎች ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ አቅርቧል።

ዘገባው በኤርትራ ላይ እንደሀገር የቀረበ ሳይሆን፤ በተናጠል መሪዎች የፈጸሟቸውን የግለሰብ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ያተኮረ ነው። በተለያዩ ሀገሮች የመብት ይዞታዎች ላይ የሚቀርቡ ዘገባዎች የተለመዱ ቢሆንም፤ የአጣሪ ኮሚሽኑ ዘገባ ግን፤ መሪዎቹ በዓለም አቀፉ የወንጅል ፍርድ ቤት ICC ወይንም በሌሎች ችሎቶች እንዲታይ የሚጠይቅ ነው።

የአጣሪ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ማይክ ስሚት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በዚህ ሳምንት ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል። በዚህ ውሳኔ ጉዳዩን ወደ ተ.መ.ድ. የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በመምራት፤ ባለስልጣናቱ ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚደረግበትን መንገድ እያፈላለጉ መሆኑን አስታውቀዋል።

“ጉዳዩ ለጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት እንዲተላለፍ ጠይቀናል። በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ICC ክስ እንዲመሰረት የመጠየቅ ስልጣን ያለው የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ብቻ ነው። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ይህንን ጥያቄ በውሳኔ ያጸድቃል ወይ? ስለዚህ የማውቀው ነገር የለም። ያን ባያደርጉ ወይንም አድርገውትም ቢሆን ሌሎች አማራጮች አሉ። የአፍሪካ ህብረት በጉዳዩ ላይ ተጠያቂነት እንዲኖር ልዩ ችሎት እንዲያቋቁም ጠይቀናል።”

በቅርቡ በሂሴን ሃብሬ ላይ በልዩ ፍርድ ቤት የተመሰረተው ክስና የጥፋተኝነት ውሳኔ ለዚህ ሂደት እንደ ምሳሌ ሊሆን ይችላል ብለዋል ማይክ ስሚት። ለመሆኑ የትኞቹ የኤርትራ ባለስልጣናት ናቸው እንዲከሰሱ የተጠየቀው በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ አስቀድሞ የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስም የተጠቀሰ ቢሆንም በማክሰኞ ዘገባ ግን ስማቸው አልተጠቀሰም። ይሄ ያልተደረገበትን ምክንያት ሲያስረዱ ክሱ የቀረበባቸው ግለሰቦች መብትን ለመጠበቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

“ድርጊቱን ፈጽመዋል ብለን የምናስበው ሰዎችን ለማነጋገር አልቻልንም። የነርሱን ምላሽና በበኩላቸው ጉዳያቸውን የሚያስረዱበት መንገድ ስላልተመቻቸ ስማቸውን ከመጥቀስ ተቆጥበናል። ይሄ እንግዲህ ፕሬዝደንቱንም ያካትታል።”

በዝርዝር የተካተተው ማስረጃ አቃቢ ግጎች ክስ ለመምስረት ከወሰኑ፤ ለምርመራ መነሻ መረጃ ሊሆን እንደሚችል ሊቀመንበሩ ገልጸዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የኤርትራ የሰብዓዊ መብት አጣሪ ቡድን ሊቀመንበር ማይክ ስሚት ዘገባቸውን የሚቃወሙና የሚደግፉ ሰልፎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ በተቃውሞ 45ሽህ የአቤቱታ ደብዳቤዎችን የተቀበሉ ሲሆን፤ ሁሉንም አንብበው፤ ወደ 500 ለሚሆኑት በስልክ ተጨማሪ መረጃ መቀበላቸውን ይናገራሉ። አንዳንዶቹ በተናገሩት ሲጸኑ፣ ሌሎች ደግሞ፣ ጻፉ ተብለን ነው፣ ሌሎች ደግሞ ከሀገር ለመውጣት እንዲረዳን በማሰብ ነው የሚሉ በርካታ ምላሾችን ማግነታቸውን አስረድተዋል።

የኤርትራዊያን ተቃውሞ በአዲስ አበባ
የኤርትራዊያን ተቃውሞ በአዲስ አበባ

“ለሁለቱም ወገኖች የምለው በነጻ ሃገር ሆነው፤ ትክክል ነው ብለው ለሚያስቡለት አላማ ሰልፍ መውጣታቸው መልካም ነገር መሆኑን ነው። ሁለቱንም ወገኖች በእጅጉ እናከብራለን።”

የኤርትራ መንግስት በአጣሪ ኮሚሽኑ የቀረበበት ውንጀላ በርእዮተ-ዓለም የተመራና የዓለም አቀፍ ተቋማትን ስልጣን የተላለፈ ነው ሲል ውድቅ አድርጎታል።

ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡ።

የመንግስታቱ ድርጅት የኤርትራ መሪዎችን ጉዳይ ወደ አለምአቀፍ የወንጀሎች ፍርድቤት ይልክ ይሆን?
please wait

No media source currently available

0:00 0:18:40 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ
የተመድ መርማሪ ኮሚሽን ሪፖርት
please wait

No media source currently available

0:00 0:01:50 0:00

XS
SM
MD
LG