የዩናይትድ ስቴትስ የስለላ ድርጅት ሲ አይ ኤ (CIA) ዳይሬክተር ጆን በርናን (John Brennan) መስሪያ ቤታቸው በቀጣይ ፕሬዚደንት ቢታዘዝም እንኩዋን እስረኞችን ውሃ ውስጥ የሰጠሙ እንዲመስላቸው በሚያደርገው የዋተርቦርዲግ (Waterboarding) ተብሎ በሚጠራው የምርመራ ዘዴ እንደማይጠቀም ተናገሩ።
ዳይሬክተር በርናን ትናናት ዕሁድ በከፊል በተላላፈው ለኤን ቢ ሲ (NBC) ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ መጠይቅ “አንድም የ ሲ አይ ኤ (CIA) መኮንን ዋተርቦርዲንግ ወይንም ውሃ ውስጥ የሰጠሙ በሚመስል ስሜት የማሰቃየት ምርመራ እንዲያካሂድ አልስማማም" ብለዋል። የማልስማማው ተቋማችን በጽናት መዝለቅ ስላለበት ነው ሲሉ አክለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከደረሱትና ቁጥሩ ወደሶስት ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ከገደሉት የሽብርተኝ ጥቃቶች በኋላ በቀጠሉት ዓመታት ሲ አይ ኤ (CIA)ተጠርጣሪ ሽብርተኞች አሜሪካ ላይ ለማድረስ ስለሚጠነሰሱ የጥቃት ሴራዎች መረጃ እንዲጠቁሙ ለማስገደድ ከባድ የምርመራ መንገዶችን መጠቀም መጀመሯ ይታወሳል። ከዚያም ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ተመርጠው ስልጣን እንደያዙ አብዛኛው የምርመራው ዘዴ ሰቆቃ ከመፈጸም የሚቆጠር ነው በማለት አግደውታል።
ሪፑብሊካን ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ ሽብርተኞችን ለማስቆም ማናቸውንም ህጋዊ መንገድ እጠቀማለሁ፣ ነገር ግን ጦር ሰራዊቱም ሆነ ሌሎች ህግ እንዲጥሱ ትዕዛዝ አልሰጥም ብለዋል። ቀደም ብሎ ግን ትራምፕ በማስጠም ስሜት ከማስጨነቅም የባሰ የምርምራ ዘዴ እደግፋለሁ ብለው ነበር።
የሳቸው ዋና ተፎካካሪ ቴድ ክሩዝ በበኩላቸው “የሀገራችንን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስፈልገውን ማናቸውንም ከባድ የምርምራ ዘዴ እንደገና ስራ ላይ አውላለሁ" ብለዋል።