የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት እለትን ምክንያት በማድረግ ያነጋገርናቸዉ የHuman Rights Watch የአፍሪቃ ፕሮግራም ሃላፊ አቶ ዳንኤል በቀለ ዘንድሮ በአፍሪቃ የተገኙ የመብትና የዴሞክራዲ ድሎችን በተለይ በኢትዮጵያና ኤርትራ ጭምር አሁንም አሉ የሚሉዋቸዉን ችግሮች ገልጸዉልናል።
ባለፈዉ ዓመት በመብትና ዴሞክራሲ አያያዝ በአንዳንድ ከሰሃራ በረሃ በታች ባሉ የአፍሪቃ አገሮች አዎንታዊ እርምጃዎች መኖራቸዉን ጠቅሰዉ፣ ቡርኪና ፋሶ በማሊ በደቡባዊ አፍሪቃ አካባቢ ደግሞ በቦትስዋና፣ በሞሪሼስና ሞዛምቢክን እንደምሳሌ ጠቅሰዋል።
በምእራብ እና ምስራቅ አፍሪቃ ነዉጠኛ የሙስልም ድርጅቶች የሚያደርሱዋቸዉ ጥቃቶችና መንግስታት እነርሱን ላይ የሚወስዱት የአጸፋ እርምጃ የሕዝብን ሰብአዊ መብት የጣሰ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የተመዘገበዉ የኢኮኖሚ እድገት አዎንታዊ መሆኑን ጠቅሰዉ በነጻነት የመደራጀት፣ ሆነ የመጻፍ፣ የመናገር መንግስትን የመቃወም መብቶች እየጠበቡ መምጣታቸዉን ገልጸዋል።
የኤርትራን የሰብአዊ መብት አያያዝ ሲገልጹም ከአፍሪቃ አገሮች ሁሉ በእጅጉ የከፋ ነዉ ብለዋል የHuman Rights Watch የአፍሪቃ ፕሮግራም ሃላፊ አቶ ዳንኤል በቀለ።