የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነው ብለው በዓለም ዙሪያ ብዙ ክርስትያን ምዕመናን የሚያምኑበት የዛሬው የገና በዓል በፍልስጥዔማዊያን ይዞታ ሥር ባለችው ቤተልሄም እየተከበረ ይገኛል።
ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት የዛሬ ሦስት ሣምንት አካባቢ ባወጡት መግለጫ ኢየሩሣሌምን የእሥራኤል ዋና ከተማነት እውቅና ከመስጠታቸው ጋር በተያያዘ በተነሣው ቅሬታ ምክንያት የዛሬው በዓል መንፈስ የተቀዛቀዘ እንዲሆን መገደዱ ተዘግቧል።
ሁኔታው ያንን ያህል የደመቀ ወይም የሞቀ አለመሆኑን ለቪኦኤ የተናገሩት ፍልስጥዔማዊቱ ናሂል ባኑራ ትረምፕ ኤምባሲያቸውን ወደ ኢየሩሣሌም ለማዛወር በመወሰናቸው ምክንያት የመከፋት ድባብ የወረደባት እንደሆነ ገልፀዋል። “የእሥራኤሉ የኃይል ይዞታ አላንስ ብሎ የአሜሪካ የታከለበት ነው የሚመስለው” ብለዋል ባኑራ።
የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁም ትናንት፤ ለዋዜማው ዕሁድ ምሽት ላይ ወደ ቅድስቲቱ ከተማ ሄደው ከዚያው መልዕክት አስተላልፈዋል።
“እሥራኤል ክርስትያኖች የሚኖሩባት ብቻ ሳትሆን የሚደሰቱባትም የመሆኗ ነገር ያኮራኛል። ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። አክለውም “በሕዝቦች መካከል በሚኖር በእንዲህ ዓይነት ወዳጅነት የምናምንና ከጀርባዬ ባሉት መቅደሶች ውስጥ የሚያመልክ የእያንዳንዱን ሰው መብትም የምንጠብቅ በመሆናችን ነው” ብለዋል።
የዋሺንግተንን እርምጃ እንደሚቃወሙ ከገለፁ መሪዎች መካከል የተገኙት የካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ፍራንሲዝ ትናንት ምሽት ለዋዜማው ቫቲካን ላይ ባከናወኑት የቅዳሴና የቡራኬ ሥነ-ሥርዓት አካታችነት እንዲሰፈን መክረዋል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ