በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዐዲሱ የቻይና-አፍሪቃ የዲፕሎማሲ ጥረት እና ከኢትዮጵያ ጋራ እያጠናከረች ያለችው ግንኙነት


 የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋራ ያላትን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ አጋርነት በሚያጠናክር ዐዲስ ጥረት፣ በዛሬው ዕለት፣ በሁለትዮሽ ግንኙነቷ የማሻሻያ ግፊት መጀመሯ ተዘገበ። ይህም፣ ቤጂንግ ከዋሽንግተን ጋራ የያዘችው ፉክክር ጎልቶ በሚታይበት በስትራተጂያዊው የአፍሪቃ ክፍል የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አካል ተደርጎ ተወስዷል።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ፣ በቤጂንጉ ዓለም አቀፍ የትብብር መድረክ ላይ ለመሳተፍ እዚያው ከሚገኙት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ “ለማንኛውም ዐይነት ኹኔታ” የታለመ ያሉትን ስትራተጂያዊ አጋርነት ለመመሥረት የሚያስችል የጋራ ስምምነት መፈራረማቸውን፣ መንግሥታዊው የዜና አገልግሎት ‘ሺንዋ’ ዘግቧል።

ቻይና፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት፣ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሙዓለ ነዋይ በማፍሰስ በቢሊዮን የሚሰላ ዶላር ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች አውላለች። ጠንካራ ምጣኔ ሀብታዊ ተሳትፎዋ፣ ኢትዮጵያ በቀጣናው የቤጂንግ ስትራቴጂያዊ ተቃናቃኝ ከኾነችው ዩናይትድ ስትቴትስ ጋራ ካላት የሻከረ ግንኙነት በተቃርኖ የሚታይ ነው።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል፣ ለሁለት ዓመታት የዘለቀ ጦርነት ላካሔደችው ኢትዮጵያ፣ የኢኮኖሚ ድጋፏን ለማሳየት፣ ዐዲስ አበባ እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ2000 አንሥቶ፣ ከቤጂንግ ከተበደረችው 13ነጥብ7 ቢሊዮን ዶላር፣ ሙሉ መጠኑ ይፋ ያልተደረገ ስረዛ ማድረጓን በያዝነው ዓመት አስታውቃለች።

ይኹንና ዋሽንግተን፣ ቻይና የምትሰጠው ብድር፣ ሀገራት ከማይወ’ጡት የዕዳ ወጥመድ ውስጥ ለማስገባት፣ ኾን ተብሎ የታለመ አሠራር ነው፤ በሚል ቤጂንግን ትወነጅላለች።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG