በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከቀይ ባህር ጥቃት በኋላ የጭነት ማጓጓዣ ዋጋ ናረ


ፎቶ ፋይል፦ አንድ መርከብ በቀይ ባህር ሆዴዳህ፣ የመን እአአ ነሃሴ 5/2018
ፎቶ ፋይል፦ አንድ መርከብ በቀይ ባህር ሆዴዳህ፣ የመን እአአ ነሃሴ 5/2018

በቀይ ባህር መርከቦች ላይ የሚደርሱትን አዳዲስ ጥቃቶችን ተከትሎ የጭነት መርከቦች የማጓጓዣ ዋጋ እንደገና እየጨመረ መሆኑ ተነገረ፡፡

ከየመን የሚነሱ የሁቲ ታጣቂዎች ካለፈው ህዳር ጀምሮ በአካባቢው የሚገኙ የጭነት ማመላለሻዎችን ዒላማ አድርገዋል።

የጥቃታቸው ምክንያት ከእስራኤል ጋር እየተጋጨ ለሚገኘው የፍልስጤም እስላማዊ ቡድን ሐማስ ድጋፍ ማሳያ መሆኑን ሁቲዎቹ እንደሚናገሩ ተመልክቷል፡፡

በቅርብ ቀናት ውስጥ አዲስ የሚሳዬል ጥቃት ሲፈጸም፣ በግዙፉ የጭነት አጓጓዥ ኩባንያ ማርስክ የምትንቀሳቀስውን መርከብንም ለመጥለፍ ሙከራ ተደርጓል።

ይህ ዓይነቱ ጥቃት ብዙዎቹን መርከቦች በአፍሪካ ደቡባዊ ጫፍ በኩል በጣም ረጅም ጉዞ እንዲጓዙ በማድረጉ የማጓጓዣ ወጪያቸውን በእጅጉ እንዲጨምር ማድረጉ ተመልክቷል፡፡ በዚህ ምክንያት ካለፈው ሳምንት አንስቶ ከእስያ ወደ ሰሜን አውሮፓ የሚደረገው የጭነት ዋጋ በእጥፍ መጨመሩ ተነግሯል፡፡

ችግሩን ለመቋቋም ዋሽንግተን ዓለም አቀፍ የባህር ኃይል ግብረ ኃይል ለማሰባሰብ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ያስገኘው ውጤት መጠነኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ክሪስ ሉ የጋራ እርምጃ እንዲወሰድ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል.

አምባሳደሩ አከለውም “ኢራን እነዚህን የሁቲዎች ጥቃቶች ለረጅም ጊዜ ስተደግፍ ቆይታለች። እኤአ ከ2015 ጀምሮ ኢራን ለሁቲዎች የረዥም ጊዜ የፋይናንስ አቅርቦትን ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ የየብስ ማጥቂያ ሚሳኤሎችን፣ እንዲሁም የባህር መርከቦችን ለማጥቃት የሚያገለግሉ የባለስቲክ ሚሳዬሎችን ጨምሮ የላቀ የጦር መሣሪያ ስርዓቶችን ለሁቲዎች አስተላልፋለች።” ሲሉ ኢራንን በመንቀስ ወቅሰዋል፡፡

ከዓለም አቀፉ የኮንቴይነር ጭነት አገልግሎት አንድ ሦስተኛ የሚሆነው በስዊዝ ካናል በኩል አድርጎ በቀይ ባህር እንደሚያልፍ ዘገባው አመልክቷል፡፡ ጥቃቱ እንደ አኪያ እና ዎልማርት የሚባሉ ግዙፎቹን የዩናይትድ ስቴትስ መደብሮችን እና አከፋፋዮችን እንደሚጎዳ ተነግሯል፡፡

ይህ በቅርቡ በሸማቾች ላይ ትልቅ የዋጋ ውድነት ሊያስከትል እንደሚችልም በሮይተርስ ዘገባ ተጠቁሟል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG