ቡሩንዲ ውስጥ ከሚያዝያ 2007 ዓ.ም. አንስቶ ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በመንግሥቱ ደጋፊዎች በሰብዕና ላይ ወንጀሎች ተፈፅመው ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገለልተኛ ባለሙያዎች ዓለምአቀፍ ምርመራ እንዲከፈት ጥሪ አሰምተዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ኤክስፐርቶች አገኘን ያሉትን ጭብጥ ያካተተ ሪፖርት ዛሬ አውጥተዋል።
ግድያ፣ መድፈር፣ ሰዎችን በዘፈቀደ መያዝና ማሠር፣ ደብዛ ማጥፋት፣ ማሰቃየትና ማሳደድ የመሳሰሉ ብርቱ የመብቶች ጥሰቶች ቡሩንዲ ውስጥ ባለፉት ሰላሣ ወራት መፈፀማቸውን ሪፖርቱ መዝግቧል።
የመንግሥታቱ ድርጅት መርማሪ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ፋትሳህ ኡጌርጉዝ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል “ረገጣዎቹን ማካሄድ የተጀመረው በሚያዝያ 2007 ዓ.ም ቡሩንዲ ውስጥ ቀውስ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ሲሆን ዛሬም ሁኔታው ቀጥሏል” ብለዋል።
“በተለይ ማሰቃየት፣ መድፈርና ከሕግ ውጭ የሚካሄዱ ግድያዎች እጅግ የተንሰራፉና በተደራጀ ሁጌታ የሚካሄዱ ናቸው” ብለዋል ኡጌርጉዝ።
የአጣሪ ኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት አክለውም ቡሩንዲ ውስጥ በሰብዕና ላይ ወንጀሎች መፈፀማቸውን ለማመን የሚያስችል ምክንያታዊ መሠረት እንዳላቸው ተናግረው ስለሆነም በተጠቀሱት ወንጀሎች እና አሁን ቡሩንዲ ውስጥ እየተካሄዱ ናቸው ባሏቸው አድራጎቶች ላይ ምርመራ እንዲከፍት ለዓለአቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ጥያቄ ማስገባታቸውን ገልፀዋል።
ቀውሱ የተጫረው ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን የመወዳደር ዕቅዳቸውን ባሳወቁ ጊዜ ሲሆን ያኔ የፕሬዚዳንቱ ሃሣብ ሕገመንግሥቱን እንደሚፃረር የተናገሩ ተቀናቃኞቻቸው ተቃውሞዎችን አስነስተው ነበር።
“የወንጀሎቹ ቀንደኛ አራማጆች - አሉ ኡጌርጉዝ - የብሄራዊ ደኅንነት አገልግሎቶች፣ ፖሊስና የሃገሪቱ ጦር እንዲሁም ኢምቦኔራኩሬ የሚባለው የገዥው ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ናቸው።”
ግጭቱ የጎሣ ቃና ባይጠፋበትም በአመዛኙ ፖለቲካዊ መሆኑን አመልክተዋል ፕሬዚዳንቱ።
ኮሚሽኑ ፍተሻዎችን ለማካሄድ ወደ ቡሩንዲ እንዲገባ መንግሥቱ ባለመፍቀዱ በሪፖርቱ ውስጥ የተካተቱት ጭብጦች የተመረኮዙት ደኅንነታቸው ብዙውን ጊዜ አደጋ ላይ ካለ ሃገሪቱ ውስጥ ከሚገኙና እንዲሁም ከተሰደዱም ከአምስት መቶ በላይ ከሚሆኑ እማኞች ጋር የተደረጉ ቃለ-መጠይቆችን እንደሆነ ኡጌርጉዝ ገልፀዋል።
መንግሥቱ ከኮሚሽኑ ጋር ለመተባበር ፍቃደኛ እንዳልሆነና በተጨማሪ ለሪፖርቱም መልስ አለመስጠቱን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
ይህ ዛሬ የወጣው የኮሚሽኑ ሪፖርት በቀጣዩ ሣምንት ውስጥ ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንደሚቀርብ ተገልጿል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ