በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቡርኪና ፋሶው መሪ ወደ ቶጎ ሸሹ


ፎቶ ፋይል፦ የቡርኪና ፋሶ መሪ ሌተና ኮሎኔል ፖል ሄንሪ ዳሚባ
ፎቶ ፋይል፦ የቡርኪና ፋሶ መሪ ሌተና ኮሎኔል ፖል ሄንሪ ዳሚባ

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባቸው የቡርኪና ፋሶ መሪ ሌተና ኮሎኔል ፖል ሄንሪ ዳሚባ ትናንት እሁድ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ መስማማታቸውን የሀገሪቱ የሃይማኖት አባቶችንና የማኅበረሰብ መሪዎችን ጠቅሶ ኤኤፍፒ ዜና ወኪል ዘግቧል።

የአካባቢው የዲፕሎማሲ ምንጮች በበኩላቸው ዳሚባ ወደ ቶጎ መዲና ሎሜ መሸሻቸውን ተናግረዋል ሲል የዜና ምንጩ ጨምሮ ዘግቧል።

ከሁለት ቀናት በፊት በመፈንቅለ መንግሥት የተወገዱት ዳሚባ፣ ባለፈው ጥር ወር ነበር የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮች ካቦሬን፣ እንዲሁ በመፈንቅለ መንግስት አስወግደው ሥልጣን ላይ የወጡት።

ሌተና ኮሎኔል ፖል ሄንሪ ዳሚባ “ፍጥጫን እንዲሁም የህይወትና የሃብት ውድመትን ለማስወገድ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተስማምተዋል” ሲሉ የሀገሪቱ የሃይማኖት አባቶችና የማኅበረሰብ መሪዎች አስታውቀዋል።

በዳሚባ እና እራሳቸውን አዲሱ መሪ አድርገው በሚቆጥሩት ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ መካከል በሃይማኖት አባቶችና በማኅበረሰብ መሪዎች አማካኝነት ከተደረገ የስማ በለው ድርድር በኋላ የመጣ ውጤት መሆኑ ታውቋል።

አዲሱ መሪ ትራ ኦሬ የሀገሪቱን የመከላከያ አዛዥ ድጋፍ ማግኘታቸውንና በእስላማዊ አክራሪዎች ላይ የሚደረገውን ዘመቻ እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።

የቀጠናው የኢኮኖሚ ትብብር ማኅበር የሆነው ኢኮዋስ በበኩሉ “በቡርኪናቤው ድራማ ተሳታፊ የሆኑት ተዋናዮች ሁሉ ልዩነታቸውን በሰላም ለመፍታት መቀበላቸውን” በመልካም ተቀብለነዋል ብሏል።

ዳሚባ ሥልጣናቸውን በሰላም ለመልቀቅ ሰባት ሁኔታዎችን አስቀምጠው እንደነበር የሃይማኖት አባቶችና የማኅበረሰብ መሪዎቹ ቡድን ገልጿል። ለእርሳቸውና ለወታደራዊ አጋሮቻቸው የደህንነት ዋስትና እንዲሁም ለኤኮዋስ ቃል የገቡትና በሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ ሲቪል አስተዳደር መመለስን የተመለከተው ይገኙበታል ተብሏል።

በቡርኪና ፋሶ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው የሃይማኖት አባቶችና የማኅበረሰብ መሪዎች፣ አዲሱ የ34 ዓመት እድሜ ያላቸው መሪ ሻምበል ኢብራሂም ትራኦሬ ቅድመ ሁኔታውን ተቀብለው፣ መረጋጋት እንዲሰፍን ጥሪ አድርገዋል ብለዋል።

አዲሶቹ መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ዓርብ ዕለት የጣሉትን የሰዓት እላፊ ገደብ አንስተው የሀገሪቱን ድንበሮችንም መልሰው ከፍተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቡርኪና ፋሶ መረጋጋት እንዲሰፍን ሩሲያ ጥሪ አድርጋለች። “በቡርኪና ፋሶ ያለው ሁኔታ በአስቸኳይ ወደ መረጋጋት እንዲያመራና ስርዓት አንዲሰፍን እንሻለን” ብለዋል የክሬምሊኑ ቃል አቀባይ ድሚትሪ ፔስኮቭ።

XS
SM
MD
LG